ቀጥታ፡

ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ ለአገረ መንግሥት ግንባታ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ይበልጥ ያጠናክራል

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 26/2017 (ኢዜአ)፡-ነጻነትና እና እኩልነት ፓርቲ ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥና ለአገረ መንግሥት ግንባታ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ይበልጥ እንደሚያጠናክር የፓርቲው ሊቀ መንበር አብዱልቃድር አደም (ዶ/ር) ገለጸ።

ፓርቲው "ጠንካራ ፓርቲ፣ጠንካራ መንግሥት፣ጠንካራ አገር" በሚል መሪ ሃሳብ ሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በዓድዋ ድል መታሰቢያ እያካሄደ ነው።

በጉባኤው ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ተወካዮች፣የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ ሊቀ መንበር አብዱልቃድር አደም (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ፓርቲው ከምስረታው ጀምሮ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ፣ ሰላማዊ የፖለቲካ ባህል እንዲገነባ የድርሻውን እየተወጣ ነው።

በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ልዩነት እንደሚፈታ የገለጹት ሊቀ መንበሩ፤ ለዚህም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቅመዋል።

ለአብነትም ፓርቲው በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን እየተሳተፈ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይሄንኑ ሚና አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።

ጠንካራ ፓርቲ ጠንካራ ሀገር ለመፍጠር ትልቅ ሚና አለው ያሉት ሊቀ መንበሩ፤ ፓርቲው ራሱን በማጠናከር የአገር መንግሥት ግንባታ ስራው እንዲሳካ ሚናችንን ይበልጥ እናጠናክራለን ብለዋል።

በጉባኤው የፓርቲው ሊቀ መንበር ምርጫ የሚካሄድ ሲሆን፤በተለያዩ ምክንያቶች የተጓደሉ የፓርቲው ብሄራዊ ምክር ቤት አባላት ማሟያ ምርጫም እንደሚካሄድ ተገልጿል።

ቋሚና ተጠባባቂ የኦዲት እና ምርመራ ኮሚሽን አባላት ምርጫም የሚደረግ ሲሆን፤ የፓርቲው የተሻሻለው መተዳደሪያ ደንብም ቀርቦ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም