ቀጥታ፡

ኢንዱስትሪን ለማስፋት የግሉን ዘርፍ ያማከሉ አሰራሮችን ማዘመን ላይ ትኩረት ተደርጓል-ሚኒስትር መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 26/2017 (ኢዜአ)፡-ኢንዱስትሪውን ይበልጥ ለማስፋትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማጉላት የግሉን ዘርፍ ያማከሉ ተግባራትን ከማከናወን ባሻገር የአሰራር ስርዓቶችን ማዘመንና ማሻሻል ትኩረት ተሰጥቶታል ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን "የአምራች ኢንዱስትሪው አለም አቀፍ የኤክስፖርት ገበያ መዳረሻ አማራጮችን ማስፋትና አለም አቀፍ የንግድ ስርዓቶችን መቀላቀል" በሚል ርዕስ ጉዳይ ውይይት እየተደረገ ነው።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ዘርፉን ይበልጥ ለማስፋትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማጉላት የግሉን ዘርፍ ያማከሉ ተግባራትን ከማከናወን ባሻገር የአሰራር ስርዓቶችን ማዘመንና ማሻሻል ትኩረት ተሰጥቶታል።

ከአሁን ቀደም መንግስት በአምራች ኢንዱስትሪው የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የፖሊሲና ስትራቴጂ ለውጦችን በማድረግ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል።

ለዚህም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትልቅ አስተዋፅኦ እንደነበረው አንስተዋል።

ውይይቱ የግል ዘርፉ በስራ ሂደት ላይ የሚያጋጥማቸው እድልና ተግዳሮቶች ላይ የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ይረዳል ብለዋል።

በመድረኩ ትልቅ አቅም ያላቸው ዓለም አቀፍ ገበያዎችን መለየትና ተደራሽ የሚሆኑበት ስልቶች ላይ ውይይት ይደረጋል ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል የሚካሔደውን 3ኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖን ትናንት መርቀው መክፈታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም