116ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ምስረታ የማጠቃለያ በዓል ዛሬ ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
116ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ምስረታ የማጠቃለያ በዓል ዛሬ ይከበራል
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 26/2017 (ኢዜአ)፡-116ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ምስረታ የማጠቃለያ በዓል ዛሬ በመስቀል አደባባይ ይከበራል።
በበዓሉ ላይ ለመታደም የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አዛዦች አዲስ አበባ ገብተዋል።
በስ ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የፖሊስ ተቋማት እንዲሁም የብሪክስ አባል ሀገራት አመራሮችና ተወካዮች ይገኛሉ።
የምስረታ በዓሉ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ሲካሄድ ቆይቷል።
ከሚያዚያ 19 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም አምስተኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት አባል ሀገራት ስፖርታዊ ውድድር በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ተደርጓል።
ውድድሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ ሱዳንና ጅቡቲ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ተሳትፈዋል።
በስፖርታዊ ውድድሩ የኢትዮጵያ ፖሊስ በሁለቱም ጾታዎች አሸናፊ በመሆን የዋንጫ እና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።
በውድድሩ የሩዋንዳ ፖሊስ ሁለተኛ፣ የኬኒያ ፖሊስ ሦስተኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቀዋል።
116ኛ የኢትዮጵያ ፖሊስ ቀን በማስመልከት በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም ከሚያዚያ 23 ቀን 25 ቀን 2017 ዓ.ም የፖሊስ ሲምፖዚየምና አውደ-ርዕይ ተካሄዷል።
የኢትዮጵያን ፖሊስ ታሪካዊ አመጣጥና የተመዘገቡ ፖሊሳዊ የሪፎርም ስኬቶችን የሚያሳዩ፤ የኢትዮጵያን የፖሊስ ታሪክ፣ የፖሊስ ሪፎርም፣ የሰው ሃብት ልማት፣ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ፣ የወንጀል መከላከል፣ የወንጀል ምርመራ፣ የሠራዊት ግንባታ፣ በፖሊሳዊ ቴክኖሎጂ፣ ጤና አገልግሎት፣ የጀግኖች ማዕከል፣ አዲሱ የፌዴራል ፖሊስ የደንብ ልብስን ጨምሮ ተቋማዊ የምርታማነትና የለውጥ እርምጃዎች በማካተት ለዕይታ ቀርበው ተጎብኝተዋል።
116ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ምስረታ የማጠቃለያ በዓል በመስቀል አደባባይ በወታደራዊ ትርዒት ታጅቦ ይከናወናል።