ቀጥታ፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለግሉ ዘርፍ በተለይም ለአምራች ኢንዱስትሪው ምቹ አውድ ፈጥሯል - ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 25/2017(ኢዜአ)፦ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለግሉ ዘርፍ በተለይም ለአምራች ኢንዱስትሪው በፖሊሲ፣ በፋይናንስ አቅርቦት እና በመሰረተ ልማት ምቹ አውድ መፍጠሩን ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) 3ኛውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በይፋ ከፍተዋል።


 

የኤክስፖው አካል የሆነ የፓናል ውይይት "የኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዘመን እድሎችና ተግዳሮቶች" በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት ተካሒዷል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) በውይይቱ ላይ እንደገለጹት የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለግሉ ዘርፍ በተለይም ለአምራች ኢንዱስትሪው ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

የኢንዱስትሪ፣ የንግድና የኢንቨስትመንት ህግጋትና ፖሊሲዎች መሻሻል እንዲሁም የመሰረተ ልማት አቅርቦት ማደግ ለአምራች ኢንዱስትሪው ትልቅ አቅም ሆነዋል ነው ያሉት።

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ለግሉ ዘርፍ የተሻለ እድልን በመፍጠር የአምራች ኢንዱስትሪውን የፋይናንስ ጥያቄ የመለሰ መሆኑንም አብራርተዋል።


 

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው ገበያ መር የውጪ ምንዛሪ ስርዓት ተግባራዊ መደረጉ ለግሉ ዘርፍ በተለይም ለአምራች ኢንዱስትሪው ምቹ እድል ፈጥሯል ብለዋል።

በተጨማሪም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት በመጨመር እና የሀገር ውስጥ አምራቾችን ተወዳዳሪነት በማሳደግ ጤናማ የፋይናንስ ስርዓት እንዲዘረጋ አድርጓል ነው ያሉት።


 

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፥ የኢኮኖሚ ማሻሻያው የግሉን ዘርፍ በተለይም የአምራች ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነትና ተሳትፎ ማሳደግ ዋነኛ ግቡ መሆኑን አንስተዋል።

የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ እንዲኖር በማስቻል ጤናማና ጥራት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ማረጋገጥም እንዲሁ።

የውጭ ምንዛሬ እጥረት መፈታቱ እና ከፍተኛ የብድር አቅርቦት መኖሩ ለአምራቾች የተመቸ አውድ መፍጠሩን በመጥቀስ፥ አምራቾች ዕድሉን በመጠቀም የወጪ ንግድ ምርትን ሊያሳድጉ ይገባል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተኸልቁ፥ የግሉ ዘርፍ በሀገር ኢኮኖሚ ያለውን ሚና ለማሳደግ ካፒታል ገበያ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ሁሉን አቀፍና አካታች እንዲሆን የአምራች ኢንዱስትሪ እድገት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም ጠቅሰዋል።


 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በሰጡት ማጠቃለያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የፋይናንስ አቅርቦት ጥያቄ በመሰረታዊነት እየፈታ ነው ብለዋል።

ይህም በተኪ ምርትና ወጪ ንግድ ተወዳዳሪ የሆኑ ኢንዱስትሪዎችን በመፍጠር ለኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ግብ መሳካት ጉልህ አሰተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም