በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን በማጠናከር አገልግሎት አሰጣጥን ውጤታማ ማድረግ ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን በማጠናከር አገልግሎት አሰጣጥን ውጤታማ ማድረግ ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 25/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን በማጠናከር አገልግሎት አሰጣጥን ውጤታማ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ''ዉጤትን ማጠናከር ፤ ተግዳሮትን ማረም" በሚል መሪ ሃሳብ ከሚያዝያ 23 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ሲያካሂድ የቆየው ምክክር ተጠናቋል።
በአፍሪካ አመራር የልህቀት አካዳሚ ሲካሄድ የቆየው የምክክር መድረክ የተቋሙ አመራሮች የተሳተፉበት ነው።
በማጠናቀቂያው ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ታደለ ቡራቃ(ዶ/ር) እንዳሉት የምክር ቤቱ አባላት ከመራጩ ህዝብ ጋር ባደረጉት ውይይት ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል የመድኃኒት አቅርቦትና አስተዳደር ጋር የተያያዙ ይገኙበታል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዘመኑን የዋጀ ተቋማዊ ስርዓት ለመገንባትና አሰራሩን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የጀመረውን ስራ ውጤታማ ለማድረግ ጠንክሮ መስራት አለበት ብለዋል።
የተጀመረው የሪፎርም ስራ ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ መስጠት የሚያስችል እንዲሆን ለራሴና ለተግባሬ መሪ ነኝ የሚል ተቋማዊ ስርዓት መገንባት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
የተሻሻሉ ህጎችንና አሰራሮችን በመከታተል በኩል ምክር ቤቱ ድጋፍ ሲያደረግ መቆየቱን ገልፀዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው ተቋሙ በአዋጅ ዝግጅት፣ አሰራርን በማዘመንና የተለያዩ ሪፎርም በመስራት ያከናወናቸው ተግባራት ውጤት እያስመዘገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለ አገር ለማውረስና ነገን መስራት የሚቻለው ዛሬ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ትናንት የነበሩ ወረቶችን ከዘመኑ ጋር በማቀናጀት በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
በተቋሙ ራዕይን ማወቅ፣ ጠንካራ የሪከርዲንግ ስርዓትና ተጠያቂነትን ማስፈን አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለቱን ለማሳለጥ የዲጂታል አሰራርን የመዘርጋትና አገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻል የሚችሉ የህግ ዝግጅት ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል ።
የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን በማጠናከር አገልግሎት አሰጣጥን ውጤታማ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ነው የጠቀሱት።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብድልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው በተሻሻለው አዋጅ መሰረት የመድኃኒት ፍላጎት ውል በተገባለት የአቅርቦት ስርዓት መሰረት የሚመራ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም በአገልግሎቱና በጤና ተቋማት በሚደረግ ስምምነት መሰረት መድኃኒት ማቅረብ የሚያስችልና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚረዳ መሆኑን ገልፀዋል።