ኢትዮጵያን በአምራች ኢንዱስትሪ የበለፀገች ሀገር የማድረግ ህልማችን የሚሳካበት ጊዜ ሩቅ አይደለም - ሚኒስትር መላኩ አለበል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን በአምራች ኢንዱስትሪ የበለፀገች ሀገር የማድረግ ህልማችን የሚሳካበት ጊዜ ሩቅ አይደለም - ሚኒስትር መላኩ አለበል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 25/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እስከአሁን የተመዘገበው ውጤት ኢትዮጵያን በአምራች ኢንዱስትሪ የበለጸገች ሀገር የማድረግ ህልማችን የሚሳካበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ ያመላከተ ነው ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሦስተኛውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በይፋ ከፍተዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም አድጓል።
ኢትዮጵያ ለአምራች ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ትኩረት መስጠቷን ጠቁመው፤ በዚህም በተሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶች መምጣታቸውን ነው ያነሱት።
በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው እንዲሁም በአስር ዓመቱ የልማት እቅድ የተያዙ የዘርፉ ግቦችም እየተሳኩ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ባለፉት ሶስት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት የተገኘው ውጤት ኢትዮጵያን በአምራች ኢንዱስትሪ የበለጸገች ሀገር የማድረግ ህልማችን ሩቅ እንዳልሆነ ያመላከተ ነው ብለዋል።
በንቅናቄው የተገኙ ውጤቶችን ማስቀጠልና አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ስራ ማስገባት በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራም ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
በተለይም የገጠር የመስኖና የኤሌክትሪክ ሃይል ችግሮችን የሚፈቱ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።
ስትራቴጂክ ጠቀሜታ ያላቸው ተኪ ምርቶችን ለሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች የሚደረገው ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያረጋገጡት።
ለአምስት ቀናት በሚካሄደው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ 288 ኢንዱስትሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን፤ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ይፈፀማል ተብሎ ይጠበቃል።
ከ120ሺህ በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች እንደሚጎበኙትም ተገምቷል።