የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ 13ሺህ 800 አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ ገብተዋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ 13ሺህ 800 አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ ገብተዋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 25/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ 13ሺህ 800 አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 3 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ተኪ ምርቶች በሀገር ውስጥ መመረታቸውንም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) 3ኛውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ መርቀው ከፍተዋል።
በኤክስፖው በሰባት የተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ 288 አምራቾች ምርቶቻቸውን አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ፤ አምራች ኢንዱስትሪዎች የልማት ትስስር ማዕከል በመሆን የኢትዮጵያን የለውጥ ጉዞ እያፋጠኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለያዩ ዘርፎች ወደ ስራ የገቡ ፋብሪካዎችም የተሻለ የወጪ ንግድ ገቢ እንዲገኝ ማስቻላቸውን ነው ያብራሩት።
ለአብነትም በወርቅ ምርት ላይ ዘመናዊ ፋብሪካዎችን ስራ በማስጀመር ጭምር በበጀት ዓመቱ አስር ወራት ከወርቅ ወጪ ንግድ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ገቢ መገኘቱን አንስተዋል።
ይህም ወርቅ በወጪ ንግድ ገቢ መጠን ለመጀመሪያ ጊዜ ቀዳሚውን ስፍራ እንዲይዝ ማድረጉን ነው የገለጹት።
የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ወደ ስራ በማስገባትም ከሀገር ውስጥ ባሻገር የሲሚንቶ ምርትን ወደ ውጪ ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አማካኝነት በሌሎች ዘርፎችም ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
ንቅናቄው ከተጀመረ ወዲህ ባሉ ጊዜያት የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከነበረበት 46 በመቶ ወደ 61 በመቶ ማደጉንም ተናግረዋል።
በተጨማሪም 13ሺህ 800 አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ስራ አቁመው የነበሩ 830 ፋብሪካዎችን ወደ ስራ መመለስ መቻሉንም ጠቁመዋል።
በዘንድሮው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት 3 ቢሊዮን ዶላር ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መመረታቸውን ገልጸዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በሀገር ውስጥ ያለው የገበያ ድርሻ እያደገ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በሀገር ውስጥ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ የኢነርጂ ፍላጎት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ይህን ፍላጎት ለመመለስ ከጸሃይ ብርሃን ሃይል ማመንጨት የሚችሉ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ስራዎች መጀመራቸውን ነው የገለጹት።
በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተገኘው ስኬት ፈተናዎችን በመቋቋም ጭምር የተመዘገበ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቀጣይም መፍትሄ ተኮር ስራዎችን በማስፋት የተጀመረው ጉዞ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።