በምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት አባል ሀገራት የስፖርት ውድድር ፍፃሜ ለመታደም የመጡ የፖሊስ አዛዦች ብሔራዊ ቤተመንግሥትን ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት አባል ሀገራት የስፖርት ውድድር ፍፃሜ ለመታደም የመጡ የፖሊስ አዛዦች ብሔራዊ ቤተመንግሥትን ጎበኙ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 25/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፖሊስ የተመሰረተበትን 116ኛ ዓመት በዓልን በማስመልከት በተዘጋጀ 5ኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት አባል ሀገራት የስፖርት ውድድር ፍፃሜን ለመታደም ከተለያዩ ሀገራት የመጡ የፖሊስ አዛዦች ብሔራዊ ቤተ መንግሥትን ጎበኙ።
የኢትዮጵያ ፖሊስ የተመሰረተበትን 116ኛ ዓመት በማስመልከት 5ኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት አባል ሀገራት ስፖርታዊ ውድድር ከሚያዚያ 19 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ በተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች እየተካሄደ ይገኛል።
በዓሉን በማስመልከት በተዘጋጀው የስፖርት ውድድር ፍፃሜን ለመታደም ከተለያዩ ሀገራት የመጡ የፖሊስ አዛዦች ዛሬ ብሔራዊ ቤተ መንግሥትን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም በቤተ መንግስቱ የሚገኙ የተለያዩ ታሪካዊ ቅርሶችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት ፕሬዚዳንት የሩዋንዳ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ጄኔራል ፌሊክስ ናሙሆራንዬ በዚሁ ወቅቱ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሙዚየሙ አስደናቂ፣ አስተማሪ፣ በጣም ጠቃሚ ታሪክ ያለበት እንዲሁም የአፍሪካ ሀገራትን ታሪክ በአንድ ቦታ የያዘ ነው።
ይህን አስተማሪ ታሪክ የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት አባላት የኢትዮጵያን ታሪክ በማየታቸው ደስተኛ መሆናቸውንም ተናግረዋል።