ቀጥታ፡

የሀገርን ዳር ድንበር፣ ክብርና ሉዓላዊነት የሚያስጠብቅ ብቁና ጠንካራ ሰራዊት ተገንብቷል - ሌተናል ጀነራል መሐመድ ተሰማ

ሚያዝያ 25/2017(ኢዜአ)፦ የሀገርን ዳር ድንበር፣ ክብርና ሉዓላዊነት የሚያስጠብቅ ብቁና ጠንካራ ሰራዊት መገንባቱን የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል መሐመድ ተሰማ ገለጹ።

ከክፍለ ጦር እስከ ጓድ ያሉ የምስራቅ ዕዝ አመራሮች የመሪነት ሚና እና ተያያዥ ወታደራዊ አቅሞችን የሚያጎለብቱ ስልጠናዎችን በብርሸለቆ መሰረታዊ ውትድርና ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለወራት ተከታትለው አጠናቀዋል።


 

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል መሐመድ ተሰማ፤ የሀገርን ዳር ድንበር፣ ክብርና ሉዓላዊነት የሚያስጠብቅ ብቁና ጠንካራ ሰራዊት ተገንብቷል ብለዋል።

የሰራዊቱ አመራሮች ብቃት በተለያዩ ወታደራዊ እውቀቶችና ቴክኖሎጂዎች በመገንባቱ በየትኛውም ግዳጅና ተልዕኮ በብቃት የመምራትና የመፈጸም አቅም በአስተማማኝ መልኩ ተገንብቷል ነው ያሉት።

እንደ አጠቃላይ የሰራዊቱ ጀግንነት፣ የመፈፀም አቅም እና የሀገር ሉዓላዊነት የመጨረሻ ምሽግ በመሆን አስተማማኝ ቁመና ላይ የሚገኝ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያን ሰላምና እድገት የማይፈልጉ የውጭና የሀገር ውስጥ ጠላቶች መኖራቸውን አንስተው በየትኛውም መልኩ የሀገሩን ሰላምና ሉዓላዊነት በጀግንነት ማስከበር የሚችል ሰራዊት መኖሩን አስረድተዋል።

ሀገር የማፍረስ ዓላማ በመያዝ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው ፅንፈኛ ሃይል ላይ ጠንካራ እርምጃ በመውሰድ እቅዱን ማክሸፍ መቻሉንም አንስተዋል።

የአመራር ኮርሱን የወሰዱ ወታደራዊ አመራሮችም ከመቼውም ጊዜ በላይ በጀግንነት የሀገርን ክብር፣ ሉዓላዊነትና አንድነት ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም