ኢትዮጵያ ለኮሪያ ሪፐብሊክ ነፃነት የከፈለችው መስዋዕትነት ለዘመናት የዘለቀውን የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያጠናክር ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለኮሪያ ሪፐብሊክ ነፃነት የከፈለችው መስዋዕትነት ለዘመናት የዘለቀውን የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያጠናክር ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 25/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለኮሪያ ሪፐብሊክ ነፃነት የከፈለችው መስዋዕትነት ለዘመናት የዘለቀውን የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ጁንግ ካንግ ገለጹ።
74ኛው የኮሪያ ዘማቾች መታሰቢያ ክብረ በዓል በኮሪያ ዘማቾች መታሰቢያ ፓርክ በተለያዩ መርኃ ግብሮች ተከብሯል።
በመርኃ ግብሩ የዘማች ቤተሰቦች፣ አርበኞች፣ የኮሪያ ዘማቾች ማህበር አባላት፣ በወቅቱ ጦራቸውን ወደ ኮሪያ የላኩ መንግስታት ወታደራዊ አታሼዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅት በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ጁንግ ካንግ እንደተናገሩት፤ ከ74 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ወታደሮች ለኮሪያ ሰላምና ነፃነት ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል።
የተከፈለው መስዋዕትነት ኮሪያ ሪፐብሊክ ወደ ነበረችበት ሰላምና ደህንነት እንድትመለስ ከማድረግ ባለፈ አሁን ለደረሰችበት እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በኮሪያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለነበራት ተሳትፎ የኮሪያ ሪፐብሊክ መንግስትና ህዝብ ትልቅ ክብርና ምስጋና እንዳለውም ተናግረዋል፡፡
በታሪክና በመስዋዕትነት የተሳሰረውን የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ሁለቱ ሀገራት በባህል፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና መሰል ስራዎች ያላቸውን ቅንጅታዊ አሰራር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ለማጠናከር በትብብር የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ኮሪያ ዘማቾች ማህበር ሊቀ መንበር ኮሎኔል እስጢፋኖስ ገብረመስቀል በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ለኮሪያ ሪፐብሊክ ነፃነትና ሰላም የከፈለችው መስዋዕትነት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የሚኖር አኩሪ ታሪክ ነው።
በጀግኖች አባቶቻችን የተጻፈው ደማቅ ታሪክ፤ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ያላትን ተደማጭነትና ተፈላጊነት ያጎለበተ ነው ብለዋል።
ተልዕኮው የኮሪያ ሪፐብሊክን ሰላም ከማስጠበቅ በዘለለ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ወዳጅነት ያጠናከረ መሆኑ ነው የገለጹት።
አዲሱ ትውልድ ቀደምት አባቶች በመስዋዕትነት ያስረከቡትን ሀገር ሰላሟን ከማስጠበቅ ባሻገር ልማቷን ማፋጠን ይጠበቅበታል ነው ያሉት።