ቀጥታ፡

ከትውልድ ግንባታ ስራችን ባለፈ ለሰላምና ልማት የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ ነን - መምህራን

ደብረ ብርሃን ፤ሚያዚያ 25/ 2017 (ኢዜአ)፡- ከትውልድ ግንባታ ስራቸው ባለፈ በከተማዋ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን በደብረ ብርሃን ከተማ መምህራን ተናገሩ።

"የጥፋት እጆችና መዘዞቻቸው" በሚል መሪ ሃሳብ በከተማዋ ሰላም ጉዳይ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ ተካሄዷል።

የውይይቱ ተሳታፊ መምህራን ከትውልድ ግንባታ ስራችን ባለፈ በከተማዋ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከመምህራኑ መካከል መምህር አባይ እሸቱ፣ መምህር ንጉስ ደስታ እና መምህርት እታፈራሁ ጌታቸው፤ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማትና የኢንቨስትመንት ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ከትውልድ ግንባታ ስራቸው ባለፈ ልማቱን በማገዝና ሰላምን ለማጽናት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በወቅታዊ ችግሮች ምክንያት በአንዳንድ አካባቢዎች የተጎዳውን የትምህርት ዘርፍ በመደገፍ ህፃናት ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የመምህራን፣ ወላጆችና አጠቃላይ የማህበረሰቡ እገዛ ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ መቅደስ ብዙነህ፤ የልማት ስራዎችን ከማጠናከር በተጓዳኝ የትምህርት ዘርፉን ጥራትና መስፋፋት እውን ማድረግ ይገባል ብለዋል። 

በዚህ ረገድም የመምህራን ሚና ወሳኝ መሆኑን አንስተው ከትውልድ ግንባታ ባለፈ ለሰላምና ልማት የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ ነን ሲሉም አረጋግጠዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የደብረ ብርሃን ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሰለሞን ጌታቸው፤ በእውቀት የዳበረ ትውልድ ከመፍጠር ባለፈ ሀገራዊ አንድነትንና አብሮነትን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የመምህራን ሚና የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማዋ የልማትና የኢንቨስትመንት ስራዎች በተጠናከረ መልኩ መቀጠላቸውን አንስተው ይህንን ለማደናቀፍ በሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ኃይል ላይ የተቀናጀ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል።

የመንግስት ሰላምን የማስፈን ቁርጠኝነት፣ የህብረተሰቡ ጠንካራ ትብብር ታክሎበት በደብረ ብርሃንና በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም