ቀጥታ፡

በፕሮጀክቱ በክልሉ የሚገኙ ሶስት ከተሞች የስራ ላይ ተለማማጅ ወጣቶችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው

ጎንደር ፤ሚያዚያ 25/2017 (ኢዜአ)፡- በ'ብቃት የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ ፕሮጀክት' በአማራ ክልል በጎንደር፣ በባህርዳርና በኮምቦልቻ ከተሞች የስራ ላይ ተለማማጅ ወጣቶችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮው አስታወቀ፡፡

ቢሮው በጎንደር ከተማ ፕሮጀክቱን ለ3ኛ ጊዜ ለማስጀመር የሚያስችል የአጋር አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ዛሬ አካሄዷል፡፡

በቢሮው የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ጥላሁን ጌታነህ እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ በጎንደር፣ በባህርዳርና በኮምቦልቻ ከተሞች በመተግበር ላይ ይገኛል ብለዋል።

በሁለት ዙር በተካሄደው የፕሮጀክቱ ትግበራም ከአሁን ቀደም በሶስቱ ከተሞች ከ6 ሺህ 500 በላይ ወጣቶችን ቋሚ የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በዘንድሮ ዓመትም ለ3ኛ ጊዜ በሚካሄደው የፕሮጀክቱ ትግበራ 3 ሺህ 258 ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የምዝገባና የምልመላ ስራ መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

ከ900 በላይ የግል ድርጅቶችም ወጣቶችን ተቀብለው የስራ ላይ ልምምድ ለመስጠት ፈቀደኛ መሆናቸውን ጠቁመው በቀጣዩ ወር ወደ ተግባር እንደሚገባም አስረድተዋል።

በጎንደር ከተማ በሁለት ዙር በተካሄደው የፕሮጀክቱ ትግበራ 3 ሺህ የሚጠጉ ወጣቶች ቋሚ የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን የገለጹት ደግሞ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ስራና ስልጠና መምሪያ ኃላፊ አቶ ላቂያው አንዳርጌ ናቸው፡፡


 

በዘንድሮ ዓመትም 1 ሺህ 482 የከተማው ወጣቶች ፈቃደኛ በሆኑ 748 የግል ንግድ ድርጅቶች ለ6 ወራት የስራ ላይ ልምምድ እንዲያካሄዱ እየተሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

በከተማው የሽመና ድርጅት አቋቁመው የሚሰሩት ወይዘሮ መቅደስ ገበየሁ እንዳሉት በሁለት ዙር 39 ወጣቶችን በሽመና፣ በማቅለምና በፈትል ሙያ የስራ ላይ ልምምድ አድርገው መቅጠራቸውን ተናግረዋል።

አባይ የቤትና የቢሮ እቃዎች ማምረቻ ድርጅት ተወካይ ወይዘሪት ስመኝ አበበ በበኩላቸው ድርጅቱ ከስራና ስልጠና መምሪያው የተላኩለትን  ስድስት ወጣቶች በእደ ጥበብ ሙያ በማሰልጠን መቅጠሩን ገልጸዋል።


 

ፕሮጀክቱ በመላ ሀገሪቱ በ11 ከተሞች እየተተገበረ እንደሚገኝም የተገኘው መረጃ ጠቁሟል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም