ቀጥታ፡

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሠራተኞች ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ቦንድ ገዙ

ጂንካ፤ ሚያዝያ 25/2017(ኢዜአ)፦ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ቦንድ ገዝተዋል።

የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በየትኛውም መልኩ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያውያንን ከዳር እስከዳር ተሰባስበው እየገነቡት ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አሁን ላይ እየተገባደደ ይገኛል።

የግድቡ ቀሪ ሥራዎች ተጠናቀው ለተሟላ አገልግሎት እስከሚበቃ ድረስ የህብረተሰቡ ድጋፍና እገዛ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በዚሁ መሰረትም የጂንካ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ለግድቡ ግንባታ የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዥ ፈፅመዋል።

ከዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች መካከል የፋይናንስ ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ንብረት ፍቃዱ፤ ለግድቡ ያደረጉት ድጋፍ የአሁኑ የመጀመሪያ እንዳልሆነ አስታውሰው ቀደም ሲልም በቦንድ ግዥ እና በሌሎች የድጋፍ አማራጮች ሲሳተፉ እንደነበር ገልጸው አሁንም በቦንድ ግዥው ላይ መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

ሌላኛው ቦንድ የገዙት አቶ አሸብር መንግሥቱ እና አቶ በርገና አንጀሎ ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ ሥራ የመንግስትን ጥረትና ቁርጠኝነት አድንቀው ቦንድ በመግዛት ድጋፋቸውን ማሳየታቸውን ገልጸዋል።

አብሮነትና አንድነታችንን በማጠናከር በሕዳሴ ግድብ ላይ ያስመዘገብነውን ድል በሌሎች የልማት ስራዎች ለማስቀጠል ዝግጁ ነን ሲሉም አረጋግጠዋል።

በቦንድ ርክክቡ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ኩሴ ጉድሼ(ዶ/ር)፤ የህብረ ብሔራዊ አንድነት ማሳያ እና የጋራ ታሪካችን መገለጫ ለሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሠራተኞች አጋርነታቸውን በማሳየታቸው አመስግነዋል።

በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥም የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ መንግስት ያሳየው ቁርጠኝነትና የህዝቡ ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይም የግድቡ የግንባታ ሥራ እስኪጠናቀቅ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በገንዘብ፣ በእውቀትና በሌሎች አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ድጋፋቸው እንደማይለይም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም