ቀጥታ፡

ከለውጡ በኋላ በተከናወኑ የማሻሻያ ስራዎች ድርጅቱን በፈጣን መልዕክት አገልግሎት ቀዳሚ ከሆኑ አስር ሀገራት ተርታ ማሰለፍ ተችሏል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 25/2017(ኢዜአ)፦ ከለውጡ ወዲህ በፖስታ አገልግሎት ዘርፍ በተከናወኑ የማሻሻያ ስራዎች ድርጅቱን በፈጣን መልዕክት አገልግሎት ቀዳሚ ከሆኑ አስር ሀገራት ተርታ ማሰለፍ መቻሉን የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ ዳግማዊ ሀይልዬ ገለጹ።

አቶ ዳግማዊ ሀይልዬ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተካሔደው የሪፎርም ስራ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የፖስታ አገልግሎት መስጠት መቻሉን አስረድተዋል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት በፈጣን መልዕክት የፖስታ አገልግሎት ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደነበረችም አስታውሰዋል።

በዋናነት በጥናት ላይ የተመሰረቱ ማሻሻያዎች በመደረጋቸው ሰፊ ለውጥ በማምጣት ድርጅቱን በፈጣን መልዕክት አገልግሎት ቀዳሚ ከሆኑ አስር ሀገራት ተርታ ማሰለፍ ተችሏል ብለዋል።

በፋይናንስ በኩል ሪፎርሙ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ተቋሙ ኪሳራ ውስጥ እንደነበር ገልጸው ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ሁለንተናዊ የለውጥ ስራዎች ትርፋማ መሆን ተችሏል ነው ያሉት።

በዚህም በየአመቱ እድገት በማስመዝገብ የተቋሙን ገቢ ከለውጡ በፊት ከነበረው አፈፃፀም ከሰባት እጥፍ በላይ ማሳደግ እንደተቻለ ለአብነት አንስተዋል፡፡

ድርጅቱ የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ ስትራቴጂ በመቅረጽ ያከናወናቸው የሪፎርም ስራዎች በዘርፉ ለውጥ እንዲያመጣ አድርጓል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት የመልዕክት ደህንነትን በሚገባው ደረጃ ማረጋገጥ መቻሉን ጠቅሰው በፖስታ አገልግሎት የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ከመሰረታቸው ለመፍታት አበክረን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በአለም ዓቀፍ ደረጃ 190 መዳረሻዎች እንዳሉት ከድርጅቱ ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም