መሶብ ግልጽና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች የታጠቀ ነው - ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
መሶብ ግልጽና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች የታጠቀ ነው - ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 25/2017(ኢዜአ)፦ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የደህንነት ፍተሻ ያለፉ መተግበሪያዎችን የያዘ ግልጽና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን የታጠቀ መሆኑን ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እንዲሁም ሚኒስትሮችና የፌዴራል ተቋማት አመራር አባላት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በትላንትናው እለት ጎብኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) በዚሁ ወቅት ያነጋገራቸው ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች መሶብ የመንግስት አገልግሎትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያቀላጥፍ ማዕከል መሆኑን አንስተዋል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሀብረቢ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ መንግሥት ለዜጎች ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት የመሥጠት ኃላፊነት አለበት፡፡
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የግሉ ዘርፍ ተሳተፎ ለሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ እድገት የጎላ አበርክቶ እንዲኖረው ማስቻል መሆኑንም በመግለጽ፡፡
ለዚህ ደግሞ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የግሉን ዘርፍ በንቃት ለማሳተፍ በሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም የመንግሥትን አገልግሎት ማዘመን አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ እንዳሉት የዜጎችን ቅሬታ ለመፍታትና ተሳትፏቸውን ለማጉላት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በቴክኖሎጂ ተደግፎ ሥራ ላይ ውሏል፡፡
መሶብ ተገልጋዮች ያለእንግልት የሚጠቀሙበት መሆኑን ገልጸው፤ የዲጂታል ቴክኖሎጂ እውቀቱ የሌላቸው ዜጎችንም በትጋት የሚያስተናግዱ ባለሙያዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በቀጣይም የአገልግሎቱን አይነትና ተደራሽነት በሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ በበኩላቸው መሶብ 12 የመንግስት ተቋማት በጋራ አገልግሎት የሚሰጡበት ማዕከል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህም ተቋማቱ የየራሳቸውን የአገልግሎት መስጫ ቴክኖሎጂዎችና መተግበሪያዎች ሲጠቀሙ እንደነበር ገልጸው፤ ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሲገቡ የደህንነት ፍተሻ ማስፈለጉን አንስተዋል።
በዚህም የሁሉም ተቋማት መተግበሪያዎች አስፈላጊው የደህንነት ፍተሻና ኦዲት ተደርጎላቸው ያለፉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ(ዶ/ር)፤ መሶብ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን የሚያስችልና የኢትዮጵያ የማድረግ አቅምን የሚያሳይ ማዕከል መሆኑን ነው የገለጹት።
መሶብ ተገልጋዮች በአንድ ጊዜ ሁለትና ከዚያ በላይ አገልግሎቶችን በፍጥነትና ቀልጣፋ በሆነ መልኩ ማግኘት የሚችሉበት አሰራር መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
የቱሪዝም ሚኒስቴርም በቀጣይ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን እንደሚቀላቀል ጠቁመው፤ ለዚህም አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡