ቀጥታ፡

የአህጉሪቱን እምቅ ሃብት በማልማትና ሃብት በመፍጠር በኩል እያንዳንዳችን ኃላፊነት ወስደን ልንሰራ ይገባል

ባህርዳር፤ ሚያዝያ 25/2017(ኢዜአ)፦ የአህጉሪቱን እምቅ ሃብት በማልማትና ሃብት በመፍጠር በኩል እያንዳንዳችን ኃላፊነት ወስደን ልንሰራ ይገባል ሲሉ የአፍሪካ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኒኮላስ ሙዱንግዌ ተናገሩ።

ዋና ዳይሬክተሩ የአፍሪካን አህጉራዊ እድገትና ብልጽግና ማረጋገጥ የሚያስችሉ እምቅ ሃብቶች መኖራቸውንም ገልጸዋል።

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 13ኛውን ዓለም አቀፍ የጥጥ፣ የጨርቃጨርቅና አልባሳት እሴት ሰንሰለት ጉባኤ ተካሄዷል።


 

በመድረኩ የተገኙት የአፍሪካ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኒኮላስ ሙዱንግዌ፤ አፍሪካ የመልማትና እድገቷን የማረጋገጥ እምቅ ሃብት ቢኖራትም እስካሁን አልተጠቀመችበትም ብለዋል።

በሁሉም መስኮች በአህጉሪቱ እምቅ ሃብት ስለመኖሩ ዘርዝረው በማልማትና ሃብት በመፍጠር በኩል እያንዳንዳችን ኃላፊነት ወስደን ልንሰራ ይገባል ነው ያሉት።

አፍሪካውያን አህጉራዊ አንድነቱንና የልማት ትስስሩን በማጠናከር የሚፈለገውን ስኬት ለማምጣት መዘጋጀት ይገባናል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ለችግሮቻችን ምክንያቶችን ከመደርደርና ወደ ሌሎች ከመጠቆም ይልቅ የልማቱ አካልና የችግሩ መፍትሄ መሆን አለብን ሲሉም አስገንዝበዋል።

በአፍሪካ እምቅ የተፈጥሮ ሃብትና አምራች የሰው ሃይል መኖሩን በማንሳት ለልማት በጋራ ከተነሳን እድገቱም ይሁን ውጤቱ ያለው በራሳችን እጅ ነው ብለዋል።


 

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ(ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራው ባሻገር ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር በምርምር ዘርፉ ስኬታማ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በተደረገው ምርምር ለሀገርና ለአህጉር ፋይዳ ያላቸውን የምርምርና የተግባር ስራዎች እያከናወነ መሆኑን አንስተዋል።

የመመረቂያ ጋወን አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲው በራሱ አቅም አምርቶ እየተጠቀመ መሆኑንም ለአብነት ጠቅሰዋል።


 

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ታምራት ተስፋዬ፤ የኮንፍረንሱ ዓላማ ለፖሊሲ ግብዓት የሚያገለግሉ የምርምር ውጤቶችን ለማበርከት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢንስቲትዩቱ አየተከናወነ ያለው የሰው ሃብት ልማት ከሀገርም አልፎ ለአህጉራዊ ልማትና እድገት መፋጠን ሚናው የጎላ እንደሆነ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም