በጋምቤላ ከተማ አዲስ የኤሌክትሪክ ኃይል የመስመር ዝርጋታ ሊከናወን ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ከተማ አዲስ የኤሌክትሪክ ኃይል የመስመር ዝርጋታ ሊከናወን ነው
ጋምቤላ፤ ሚያዝያ 25/2017 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ከተማ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግርን ለመፍታትና ተደራሽነትን ለማስፋት የሚያስችል አዲስ የመስመር ዝርጋታ ሊያከናውን መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
አገልግሎት መስሪያ ቤቱ በጋምቤላ ከተማ አዲስ በሚዘረጋው የኃይል መስመር ዝርጋታ ዙሪያ ከከተማው ነዋሪዎች ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል ።
በአገልግሎት መስሪያ ቤቱ የጋምቤላ ሪጅን ዳይሬክተር አቶ አማረ ገብረ መድህን፤ በጋምቤላ ከተማ የኃይል አቅርቦት አስተማማኝና ተደራሽ ለማድረግ አዲስ የኃይል መስመር ዝርጋታ ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የተከናወነው የኃይል ዝርጋታ በእንጨት ምሰሶ የተከናወነ በመሆኑ በእርጅና ምክንያት እየወደቀና የኃይል መቆራረጥ እየገጠመ መሆኑን አንስተው አሁን ላይ አዲስ የኃይል መስመር ዝርጋታ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በቀጣይ የሚዘረጋው መስመር የኃይል አቅርቦቱን ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ የሚያስችልና ለረጅም ዓመታት አገልግሎት የሚሰጥ ይሆናልም ነው ያሉት።
የውይይት መድረኩ አስፈላጊነትም ለሚከናወነው የመስመር ዝርጋታ የማህበረሰቡ ትብብርና አጋርነት እንዲኖር ለማስቻል ነው ብለዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት እና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ኡቶዉ ኡኮት፤ የኃይል መሠረተ ልማት አገልግሎቱን ማዘመንና ተደራሽነቱን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም በክልሉ ይስተዋል የነበረውን የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ ችግር በመፍታት የተሻለ አገልግሎት እንዲኖር ለማስቻል ያረጁ መስመሮችንና ምሰሶዎችን ለመቀየር በሚደረገው ጥረት አስፈላጊውን እገዛ እና ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።
በዚህ ረገድ ማህበረሰቡ አስፈላጊነቱን በቅጡ በመገንዘብ ለልማት ክንውኑ መሳካት የድርሻውን እንዲወጣ አስገንዝበዋል።
የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኡቻን ዶርጊ (ዶ/ር) በበኩላቸዉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በከተማው አዲስ የሚዘረጋዉ የኃይል መስመር ለከተማዉ እድገትና ለህዝቡ ተጠቃሚነት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም በከተማው ለሚከናወነው አዲስ የኃይል መስመር ዝርጋታ የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊዉን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በመላ ሀገሪቱ በ72 ከተሞች አዲስ ከሚዘረጉ የኃይል መስመሮች መካከል የጋምቤላ ከተማ አንዱ መሆኑም በመድረኩ ተመላክቷል።
በውይይት መድረኩ ላይ በጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ከሚገኙ አምስት ቀበሌዎች የተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና በየደረጃው ያሉ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።