የኢትዮጵያ የእንስሳት ምርትን ተወዳዳሪ ለማድረግ ያለመ ምዕራፍ ሁለት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የእንስሳት ምርትን ተወዳዳሪ ለማድረግ ያለመ ምዕራፍ ሁለት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2017(ኢዜአ)፦ጥራቱና ደህንነቱ የተጠበቀ የሥጋ ምርት ወደ ቻይና መላክን ጨምሮ የኢትዮጵያ የእንስሳት ምርትን ተወዳዳሪ ለማድረግ ያለመ ምዕራፍ ሁለት ፕሮጀክት ይፋ ተደርጓል።
ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ የእንስሳት ሀብት እሴት ሰንሰለትን ለማሻሻል የአቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል ነው።
ፕሮጀክቱ በግብርና ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ግብርና ልማት ባለሥልጣን እና በተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት/UNIDO/ በጋራ የሚተገበር ሲሆን፤ በቻይና መንግስት የሚደገፍ መሆኑም ተገልጿል።
ለሦስት ዓመታት የሚተገበረው ይሄው ፕሮጀክት በስጋ ማቀነባበር ሥራ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎችን አቅም መደገፍ፣ ከእንስሳት በሽታ ነጻ የሆኑ አካባቢዎችን መፍጠር እንዲሁም የምርት ጥራት ፍተሻ ባለሙያዎችን አቅም በመገንባት ጥራትና ደህንነቱ የተጠበቀ የሥጋ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ያለመ ነው።
ኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ወደ ውጭ የሚላከው የሥጋ ምርት በሚጠበቀው ደረጃ አለመሆን እንዲሁም ከንግድ ጋር የተተያዙ ችግሮች ከዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ እንዳንጠቀም አድርጓል።
ፕሮጀክቱ በዚህ ረገድ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት አገራዊ ፋይዳው የላቀ መሆኑንም አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ሚኒስትር ካውንስለር ሊዩ ዥዋንግ በበኩላቸው እነደተናገሩት፤ ቻይና ውጤታማ የልማት እንቅስቃሴዋን ለኢትዮጵያ ልምድ ለማካፈል ዝግጁ ናት።
ዛሬ ይፋ የሆነው ፕሮጀክትም በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል ሲሉም ተናግረዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ከፍተኛ አማካሪ ዓለማየሁ መኮንን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ጥራታቸውና ደህንነታቸው የተጠበቀ የሥጋ ምርቶች ወደ ቻይና ገበያ ለማስገባት አስፈላጊው ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።
በዚህም በፕሮጀክቱ የመጀመሪያው ምዕራፍ የቻይና ምርት ተቆጣጣሪ ተቋም የምርት ጥራት መስፈርቶችን በዝርዝር የያዘ ሰነድ መላኩን አስታውቀው፤ በመስፈርቱ መሰረት አስፈላጊው ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በዘርፉ ያሉ ባለድርሻ አካላት ወደ ቻይና ተጉዘው ከቻይና የሥጋ ኢንዱስትሪ ልምድ እንዲቀስሙ መደረጉን ጠቁመው፤ ይህም እንደ አገር ከፍተኛ አቅም የተገኘበት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀሚድ ጀማል (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በፕሮጀክቱ የመጀመሪያው ምዕራፍ ሥጋን የሚመረምሩ ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ ፕሮቶኮሎች ዙሪያ ግንዛቤ እንዲጨብጡ መደረጉን ጠቁመዋል።
በተባባሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል ተወካይ አቶ አሰግድ አዳነ እንዳሉት፤ ድርጅቱ በኢትዮጵያ የእንስሳት ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል የቴክኒክ ድጋፍን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ የሚረዱ ለፖሊሲ እና ስትራቴጂ ግብዓት የሚሆኑ የጥናት ውጤቶችን ለመንግሥት ተደራሽ እየተደረገ መሆኑም ጠቁመዋል።