መንግሥት ሀገራዊ ተቋማትን ለማጠናከር ያለው ቁርጠኝነት የጸና ነው - የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት ሀገራዊ ተቋማትን ለማጠናከር ያለው ቁርጠኝነት የጸና ነው - የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ ፣ሚያዝያ 24/2017 (ኢዜአ)፦መንግሥት ሀገራዊ ተቋማትን ለማጠናከር ያለው ቁርጠኝነት የጸና ነው ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ።
አገልግሎቱ ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ መልዕክት ያስተላለፈ ሲሆን በዚህም ከዚህ በፊት አንዳንድ ወገኖች በፈጠሩት ችግር የተነሣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ጉባኤ ለመሳተፍ ላልቻሉ ሦስት አባቶች ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን አስታውቋል።
ሀገራዊ ተቋማት ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ያላቸውን የላቀ ሚና መንግሥት ስለሚረዳ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል የተፈጠረው መለያየት እንዲፈታ መንግሥት የመሪነቱን ሚና መጫወቱን አስታውሷል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሀገር ግንባታ የነበራትንና የሚኖራትን ሚና በመገንዘብ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ሲሰጥ ቆይቷል። በዚህ አቋሙም ይቀጥላል ነው ያለው።
ይሄንን ያልተረዱ አንዳንድ አካላት ችግሮችን ፈጥረው የነበረ ቢሆንም እንኳን፣ መንግሥት ለቤተ ክርስቲያንዋ እና ለምእመንዋ ሲል በሆደ ሰፊነት ለማለፍ ወስኗል። ይሄም ከግለሰቦች ችግር ይልቅ የቤተ ክርስቲያንዋን አስተዋጽዖ ስለሚመለከት ነው።
መንግሥት ችግሩ እንዲፈታ ሲኖዶሱ ያቀረበውን ጥያቄ ተቀብሏል። በሂደቱም ተቀራርቦ መነጋገር ከሁሉም የተሻለ የመፍትሔ መንገድ መሆኑ ታይቷል ብሏል።
ስለዚህም ሲኖዶሱ መንግሥት ነገሩን በሆደ ሰፊነት እንዲመለከተው በጠየቀው መሠረት፣ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ( ዶ/ር )፣ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ (ዶ/ር) እና ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ በሲኖዶሱ ስብሰባ ለመገኘት እንዲችሉ ከመንግሥት የሚጠበቀውን ሁሉ እንደሚያደርግ የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት
በመልዕክቱ ገልጿል::
#Ethiopian_News_Agency
#Ethiopia
#ኢዜአ