ቀጥታ፡

ለክልሉ ህዝብ የመልማት ፍላጎትና የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ-ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

ሰቆጣ፤ሚያዚያ 24/2017 (ኢዜአ)፦ለአማራ ክልል ህዝብ የመልማት ፍላጎትና የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ፥ ተቋርጦ የቆየውን የጋሸና-ላሊበላ-ብልባላ-ሰቆጣ የአስፋልት መንገድ ቀሪ ስራዎች ግንባታን አስጀምረዋል።

የመንገዱ ግንባታ ሲጠናቀቅ በዋግ ኽምራ የሚገኙ እምቅ የተፈጥሮ ሃብትና የቱሪስት መስህቦችን ወደ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።

በአካባቢው በተለይም የእንስሳት፣ የማእድንና ሌሎች ሃብቶችን በጥናት ላይ ተመስርቶ በማልማት ለሀገራዊ እድገት ለማዋል የሚሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለክልሉ ህዝብ የመልማት ፍላጎትና የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉም ርእሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሃመድ አብዱራህማን፤ የጋሸና-ላሊበላ -ብልባላ-ሰቆጣ የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ከክልሉም ባለፈ ትልቅ ሃገራዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

የመንገዱ መገንባት በአካባቢው የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎችን ለመጎብኘት እንዲሁም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማቱን ለማሳለጥ ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች እየተገነቡ ያሉትን የመንገድ መሰረተ ልማቶች ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ በፍጥነትና በጥራት ለማከናወን ጥረት እየተደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ማህበረሰቡም ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት ጊዜ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅና ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ በመንከባከብ የበኩሉን ሚና እንዲወጣም አሳስበዋል።

የመንገድ ፕሮጀክቱ 204 ኪሎ ሜትርን የሚሸፍን ሲሆን በመንገዶች አስተዳደር 5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚገነባ መሆኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም