ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በዘላቂነት ለመግታት ውጤታማ ተግባራትን አከናውናለች-ሚኒስቴሩ



አዳማ፤ሚያዝያ 24/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በዘላቂነት ለመግታት የሚያስችል ውጤታማ ተግባራትን ማከናወኗን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አመለከተ።

ከፌዴራልና ከክልሎች አካባቢ ጥበቃ ሴክተሮችና ከሚኒስቴሩ የተወጣጡ የስራ ኃላፊዎች የተሳተፉበት የዘጠኝ ወራት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ምላሽ ትግበራ ዕቅድ ግምገማ መድረክ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በሚኒስቴሩ የተናበበና የተቀናጀ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ምላሽ ትግበራ ብሄራዊ አስተባባሪ ሙክታር አቡኬ (ዶ/ር) እንደገለፁት፥ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በዘላቂነት ለመግታት ውጤታማ ተግባራትን አከናውናለች።

በዚህም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል የአረንጓዴ አሻራ፣ የብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ እቅዶች ትግበራ እና በአየር ንብረት ለውጥ ለሚደርስ ጉዳት እና ኪሳራ የሚከፈል የፋይናንስ ፈንድ ማዕቀፍ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን ገልፀዋል።

በተለይ ሀብት የማሰባሰብ፣የፖሊሲ እና የማስፈፀሚያ ስትራቴጂዎች፣ አሰራሮችና የህግ ማዕቀፎችን የማበጀት ስራ በውጤታማነት መከናወኑን አንስተዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስዩም መኮንን በበኩላቸው፥ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ጉዳት እያየለ መጥቷል።

ድርቅ፣ጎርፍ፣የበረሃ አንበጣ፣የመሬት መንሸራተት በተደጋጋሚ ጊዜ እያጋጠመ መሆኑን ጠቅሰው፥ይህም በግብርና ምርትና ምርታማነት፣ በእንስሳት ሀብት፣በመሰረተ ልማትና በሀይል አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል።

ሀገሪቷ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የጀመረቻቸው አዳዲስ ኢንሺዬቲቮች ውጤታማ እንዲሆኑ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ እውን ማድረግ ላይ መረባረብ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ለዚህም የተናበበና የተቀናጀ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ምላሽ ትግበራን ውጤታማ ለማድረግ በየደረጃው ያሉ የባለድርሻ አካላት ርብርብ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

ለዚህም ሲባል መንግስት ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የተናበበና የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ፖሊሲና ስትራቴጂን በመቅረጽ እንዲሁም አሰራሮችና የህግ ማዕቀፎች እየዘረጋ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም