ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለች- አምባሳደር ሃደራ አበራ

አዲስ አበባ ፤ሚያዚያ 24/2017 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ ለአካባቢው ሰላም እና መረጋጋት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሃደራ አበራ ገለጹ።

አምባሳደር ሃደራ አበራ፥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፖለቲካ እና ሰላም ግንባታ ጉዳዮች ክፍል ውስጥ የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር አምባሳደር ግርሃም ሜላንድን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው፥ ከዳይሬክተሩ ጋር በቀጣናው ወቅታዊ የሰላም እና ደኀንነት ዙሪያ መክረዋል።

አምባሳደር ሃደራ፥ የኢትዮጵያ መንግሥት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በቁርጠኝነት እየተገበረ መሆኑን፣ የሽግግር ፍትሕ እና ሀገራዊ ምክክር በማድረግ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ተመድ ለኢትዮጵያ በሰላም ግንባታ ዙሪያ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ ለአካባቢው ሰላም እና መረጋጋት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗንም አመልክተዋል።

አምባሳደር ግርሃም ሜላንድ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በቀጣናው የተመድ ሁነኛ አጋራ መሆኗን ገልጸዋል።

በአፍሪካ ሕብረት እና በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ውስጥ ሁነኛ ቦታ ያላት ሀገር ናት ብለዋል።

በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ ያላትን ሚና አጠናክራ እንድትቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም