ቀጥታ፡

በጉባኤው ሀገራት በመሰረተ ልማት ፕሮግራሞቻቸው ዘላቂነት ያለው የስራ እድል መፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ-ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 24/2017(ኢዜአ)፦20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት አህጉራዊ ጉባኤ ሀገራት በመሰረተ ልማት ፕሮግራሞቻቸው ዘላቂነት ያለው የስራ እድል መፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።

20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት አህጉራዊ ጉባኤ ከግንቦት 11 ጀምሮ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።

ጉባኤውን አስመልክተው የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ጉባኤው ከግንቦት 11 እስከ 15/2017 ዓ. ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

"የማይበገር ማህበረሰብ እና ጤናማ አካባቢ የሰው ኃይልን በብዛት የሚጠቀሙ የኢንቨስትመንት ፕሮግራም አካሄዶች " በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚካሄድም ጠቁመዋል፡፡

ጉባኤውን የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት እና የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በጋራ ያዘጋጁት መሆኑን አንስተዋል።

በጉባዔው ፖሊሲ አውጪዎች፣የአሰሪዎች እና የሰራተኞች ማህበራት እና ሰራተኛ-ተኮር የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የአካዳሚክ እና የምርምር ተቋማት እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።

የዘርፉን ዕድሎችና ፈተናዎች የሚዳስሱ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚካሄድባቸውም ጠቁመዋል።

ጉባኤውን በስኬት ለማከናወን የተለያዩ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑን ገልጸዋል።

በጉባኤው ሀገራት በመሰረተ ልማት ፕሮግራሞቻቸው ዘላቂና ደህንነቱ የተጠበቀ የሰው ሃይልን በስፋትና በጥራት በማፍራት እንዲሁም ሰፊ የስራ እድል መፍጠር በሚያስችሉ ላይ ያተኮረ ውይይት እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

የዓለም አቀፉ የሠራተኛ ድርጅት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ካንትሪ ዳይሬክተር ኩምቡላ ንዳባ፥ ጉባኤው ሁሉን አቀፍ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማበረታታት የሚያግዝ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ስኬቶች ታሪክ ፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን ለማሳየት እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በማህበረሰብ ስራዎች እና በወጣቶች ልማት ፕሮግራሞች ላይ ያላትን የረዥም ጊዜ ተሞክሮ ለአባል ድርጅቶች ልምድ እንድታካፍል የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በበኩላቸው፥ ጉባኤው የተረጋጋ ኢኮኖሚ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን አንስተዋል።

ተሳታፊዎች በዘርፉ ልምድ የሚለዋወጡበት እንደሆነም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም