የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አሰራሩን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ጥናት እያካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አሰራሩን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ጥናት እያካሄደ ነው
አዳማ፤ ሚያዝያ 24/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አሰራሩን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ጥናት እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ።
የማስፈጸም አቅሙን ለማሳደግም ለዋና መስሪያ ቤት እና ለቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ያዘጋጀው የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና በአዳማ ከተማ እየተሰጠ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በሕግ የተደነገጉ የሰዎች መብቶችና ጥቅሞች ማረጋገጥ እንዲሁም ጥራት፣ ቅልጥፍናና ግልጽነት ያለው መልካም የመንግስት አስተዳደር መስፈኑን ለማረጋገጥ የሚሰራ መሆኑ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ስመኝ ውቤ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት ተቋሙ የሚያጋጥሙ አስተዳደራዊ በደሎች ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ ጥረት እያደረገ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት አሰራሩን በማዘመን ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ ማስደገፍ የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ መሆኑን አመልክተዋል።
ተገልጋዩ ወደ ተቋሙ በአካል መምጣት ሳይጠበቅበት ባለበት ሆኖ ያጋጠመውን የአስተዳደር ችግር ማቅረብ የሚችልበት አስቻይ ሁኔታ ለማመቻቸት ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
በተለይ ከንብረት ይገባኛል፣ ከአሰሪና ሰራተኛ ጋር የሚቀርቡ አቤቱታዎች ካለምንም ገደብ በተቋሙ እንደሚስተናገዱና እልባት እየተሰጣቸው መሆኑን አስረድተዋል።
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የተቋሙ የባህር ዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጋሻነው ደሴ ቅርንጫፉ አቅሙን ለማጠናከር ስልጠናው ገንቢ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
በእውቀትና በክህሎት ላይ የተመሰረተ አስተዳደራዊ ፍትህ የመስጠት አቅማችን ከፍ ማለት አለበት ያሉት አቶ ጋሻነው እራሳችንን እያበቃን በአዋጅ የተሰጠንን ኃላፊነት ለመወጣት አጋዥ ነው ብለዋል።