በ5ኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ስፖርት የግማሽ ማራቶን ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸነፉ - ኢዜአ አማርኛ
በ5ኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ስፖርት የግማሽ ማራቶን ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸነፉ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2017(ኢዜአ)፦ በ5ኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ስፖርት ውድድር የግማሽ ማራቶን ሩጫ ውድድር በሁለቱም ፆታዎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸናፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ 116ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን በማስመልከት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው 5ኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ስፖርት ውድድር እንደቀጠለ ነው፡፡
በዛሬው እለት መነሻና መድረሻውን ሰሚት አደባባይ በማድረግ በተካሄደው የግማሽ ማራቶን ሩጫ ውድድር የኢትዮጵያ፣ የታንዛኒያ፣ የኬንያ እና የጅቡቲ ፖሊስ አትሌቶች ተሳትፈዋል፡፡
በግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድሩ በሁለቱም ፆታዎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቀዋል፡፡
በወንዶች አዲሱ ጎበና፣ ስማቸው ወልዴ እና ባለው ይሁኔ እንዲሁም በሴቶች መሰለች አለማየሁ፣ ጋዲሲ ሙሉ እና ሹኮ ጋማሞ እንደየቅደም ተከተላቸው ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ በመውጣት አሸናፊ ሆነዋል፡፡
የውድድሩ አስተባባሪ ረዳት ኮሚሽነር ማርቆስ ገነት እንዳሉት፤ 5ኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ስፖርት ውድድር በተለያዩ መርሀ ግብሮች እየተከናወነ ነው፡፡
ውድድሩ በአትሌቲክስ፣ ቦክስ፣ ኢላማ ተኩስ፣ ዳርት፣ ቴኳንዶ እና እጅ ኳስ ዘርፎች የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ውድድሩ በቀጣናው ሀገራት መካከል ያለውን ፖሊሳዊ ትብብርና አንድነት የሚያጠናክር መሆኑንም ተናግረዋል።
የውድድሩ አሸናፊዎች አትሌት አዲሱ ጎበና እና መሰለች አለማየሁ ለውድድሩ በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
የኬንያ ፖሊስ አባል ሩጉሩ በበኩሏ ውድድሩ ጥሩ እንደነበር በዚህም ደስተኛ መሆኗን ገልጻለች፡፡