20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት አህጉራዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት አህጉራዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2017(ኢዜአ)፦ 20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት አህጉራዊ ጉባኤ ከግንቦት 11 ጀምሮ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።
ጉባኤውን አስመልክተው የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም 20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት አህጉራዊ ጉባኤ ከግንቦት 11 እስከ 15/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
"የማይበገር ማህበረሰብ እና ጤናማ አካባቢ የሰው ኃይልን በብዛት የሚጠቀሙ የኢንቨስትመንት ፕሮግራም አካሄዶች" በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚካሄድም ጠቁመዋል፡፡
ጉባኤውን የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት እና የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በጋራ ያዘጋጁት መሆኑን አንስተዋል።
በጉባዔው ፖሊሲ አውጪዎች፣ የአሰሪዎች እና የሰራተኞች ማህበራትና ሰራተኛ-ተኮር የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የአካዳሚክና የምርምር ተቋማት እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
የዘርፉን ዕድሎችና ፈተናዎች የሚዳስሱ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርቦ ውይይት እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።
ጉባኤውን በስኬት ለማከናወን የተለያዩ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑን ገልጸዋል።