በዞኖቹ በመኸር አዝመራ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብል ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኖቹ በመኸር አዝመራ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብል ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው
አምቦ/ጊምቢ፤ ሚያዝያ 24/2017(ኢዜአ)፦ በምዕራብ ሸዋ እና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች በክረምት የመኸር አዝመራ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብል ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኖቹ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤቶች ገለጹ።፡
የምዕራብ ሸዋ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ደጀን ደቡሼ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ በ2017/18 የምርት ዘመን በመኸር አዝመራ 886 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
ከሚለማው መሬትም 32 ሚሊዮን ኩንታል ለማግኘት መታቀዱን ገልጸው እስካሁን 274 ሺህ 501 ሄክታር መሬት መታረሱን ገልጽዋል።
ለምርት እድገቱም ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እየቀረበ መሆኑንም ተናግረዋል።
የምዕራብ ሸዋ ዞን የህብረት ሥራ ማህበራት ማስፋፊያ ጽህፈት ቤት የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ስርጭት ባለሙያ አቶ ዳኛቸው አለማየሁ በበኩላቸው፣ ለዞኑ ለመኸር አዝምራ 410 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና ዘጠኝ ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለወረዳዎች እየተሰራጨ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዞኑ በመኸር አዝመራ የእርሻ ልማት ከ119 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉም አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ በምዕራብ ወለጋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት የአዝርዕት ልማት እና እጽዋት ጥበቃ ቡድን መሪ እጅጋየው አስፋው በበኩላቸው በመኸር አዝመራው ከ400 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው።
በመኸር ወቅቱ 416 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያየ ሰብል በዘር በመሸፈን 13 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱንም ገልጸዋል፡፡
በተለይም በዘንድሮ የመኸር እርሻ አርሶ አደሮችን በክላስተር በማደራጀት ወደ ዝግጅት ሥራ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ቡድን መሪዋ እንደገለጹት በዞኑ ከሚለሙ ዋና ዋና ሰብሎች መካከል በቆሎ፣ ገብስ፣ ባቄላ፣ ቦሎቄና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።
በመጪው የመኸር እርሻ ልማት ከ260 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በሰብል ልማቱ እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል።
ለመኸር እርሻው 340ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች እየቀረበ ነው ያሉት ደግሞ በጽህፈት ቤቱ የምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ባለሙያ አምላክ አንዷለም ናቸው፡፡
እስካሁንም ወደ ወረዳ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ከ85 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ መድረሱን ጠቁመው ከዚህ ውስጥም ከ24 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተከፋፍሏል ብለዋል፡፡