የግብርና ምርት ውል አዋጅ ለአርሶ አደሩ የገበያ ትስስር በመፍጠር እና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ጉልህ ጠቀሜታ አበርክቷል - ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ምርት ውል አዋጅ ለአርሶ አደሩ የገበያ ትስስር በመፍጠር እና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ጉልህ ጠቀሜታ አበርክቷል - ሚኒስቴሩ

ወላይታ ሶዶ፤ ሚያዝያ 23/2017(ኢዜአ)፦ የግብርና ምርት ውል አዋጅ የአርሶ አደሩን የገበያ ትስስርና የፋይናንስ ችግር ከመፍታት ባለፈ ለቴክኖሎጂ ሽግግር ያለው ጥቅም የጎላ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ በግብርና ምርት ውል አዋጅና በእንስሳትና አሣ ሃብት ኢንቨስትመንት ላይ ያተኮረ ክልል አቀፍ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ አካሂዷል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንትና ምርት ግብይት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት የግብርና ምርት ውል አዋጅ 1289/2015 በአምራችና አስመራች መካከል ያለውን ግንኙነት ለመወሰን የወጣ ነው፡፡
አዋጁ ጸድቆ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ ባለው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለግብርና ኢንቨስትመንት መስክ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይ ለአርሶ አደሩ የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግና በዘርፉ የሚስተዋለውን የፋይናንስ ችግር ከመፍታት ባሻገር ዓለም አቀፍ አምራች ድርጅቶች እንዲሳተፉ ዕድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል፡፡
በተያዘው ዓመትም አርሶ አደሩ ከአስመራች ጋር በገባው ውል መሰረት ከ2 ሚሊዮን ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶችን ማምረቱን ገልጸዋል፡፡
በግብርና ምርት ውሉ ከተካተቱ አራት ተዋንያን መካከል በአምራችነት የሚጠቀሱ በግል፣ በቡድንና በህብረት ሥራ የተደራጁ አርሶ አደሮች ቀዳሚ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
በሀገሪቱ በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ከ6ሺህ በላይ ባለሃብቶች ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የሰብል ልማት እያከናወኑ ነው ብለዋል።
በቀጣዮቹ ዓመታትም በባለሀብቶች የሚለማን መሬት ወደ 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር ለማሳደግ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በእንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ዘርፍ ከ3ሺህ 277 በላይ ባለሃብቶች መሰማራታቸውን የጠቀሱት ደግሞ የእንስሳት እና ዓሣ ምርት ኢንቨስትመንት ምርት ግብይት ዴስክ ሃላፊ አቶ ከድር ሉባንጎ ናቸው፡፡
በባለሀብቶቹ ከሚከናወነው የእንስሳት እና አሣ ሃብት ልማት በየዓመቱ ከ10 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደሚገኝ ጠቅሰው የሌማት ትሩፋት ፕሮግራሙ በዘርፉ ለተመዘገበው ስኬት ጉልህ አበርክቶ አለው ብለዋል፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዲላ ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ሃላፊ መርሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው የግብርና ምርት ውል አርሶ አደሩን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ምርት እንዲያመርት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ወላይታ፣ ጋሞና ጎፋ ዞኖች ከ974ሺህ 850 ኩንታል በላይ የኤክስፖርት ምርቶችን ለማምረት ከአርሶ አደሩ ጋር ውል መገባቱንም ተናግረዋል፡፡
ቀይ ቦሎቄ፣ ማሾ፣ ሽምብራ፣ ሰሊጥ፣ ባቄላ እና አተር ከሚመረቱ ምርቶች መካከል እንደሚጠቀሱ ገልጸው፣ የግብርና ምርት ውሉ አርሶ አደሩ የዓለም ገበያን ጭምር በማሰብ ጥራት ያለው ምርት በማምረት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን እንዲያሳድግ ያግዘዋል ነው ያሉት።
በመድረኩ ከክልል ጀምሮ በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን በግብርና ምርት ውልና በእንስሳትና አሣ ሃብት ኢንቨስትመንት ላይ ያተኮሩ ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡