ቀጥታ፡

በጎንደር ከተማ ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ በተሻለ ጥራትና ፍጥነት እየተከናወነ ነው - አስተዳደሩ

ጎንደር፤ ሚያዝያ 23/2017(ኢዜአ)፦ የጎንደር ከተማ ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ በተሻለ ጥራትና ፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

ለሁለተኛው ምዕራፍ የጎንደር ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀስላሴን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ከቀናት በፊት በአዲስ አበባ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር መካሄዱ ይታወቃል።

የሁለተኛውን ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ክንውን በተመለከተ የከተማ አስተዳደሩ የኮሙኑኬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ አበበ ላቀው ዛሬ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም 12 ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት የእግረኛና የብስክሌት መንገዶችን ጨምሮ የአረንጓዴ ስፍራዎችና የማፋሰሻ ቦዮች ግንባታ ሥራዎች የተካተቱበት መሆኑን አንስተዋል።

የአስፋልት ማንጠፍ፣ ስማርት የኤሌክትሪክ ፖሎች ተከላን ጨምሮ የስማርት መፀዳጃ ቤቶችም የኮሪደር ልማቱ አካል ሆነው እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

የኮሪደር ልማት ሥራው ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል የፈጠረ፣ የህብረተሰቡን የሥራ ባህል የቀየረ እንደሆነና በቀን ለ22 ሰዓታት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለኮሪደር ልማቱ የህብረተሰቡ ተሳትፎና ትብብር ከፍተኛ ነው ያሉት ሃላፊው፣ የግንባታ ሥራውን በመጪው መስከረም 2018 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የከተማውን የቀደመ ታሪክና ገናና ስም በሚመጥን አግባብ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ለከተማዋ የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መነቃቃት ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ነው ያነሱት።

ከአጼ ቴዎድሮስ - አዘዞ አየር ማረፊያ የሚደርሰው ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚደረግበት መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።

ለከተማው የኮሪደር ልማት ሥራ እንዲውል በአዲስ አበባ የተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ግቡን የመታ መሆኑን ጠቁመው፣ በመርሃ ግብሩ በመሳተፍ ለከተማው እድገት የገንዘብ ድጋፍ ላበረከቱ ሁሉ በከተማ አስተዳደሩ ስም አመስግነዋል፡፡

በጎንደር ከተማ በመጀመሪያው ምዕራፍ የተካተተው የፒያሳና አካባቢው የኮሪደር ልማት ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ጥር ወር 2017 ዓ.ም ተመርቆ ለአገልግሎት መብቃቱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም