ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በሲዳማ ክልል ምርት አቋርጠው የነበሩ 64 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት ተመልሰዋል - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 23/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በሲዳማ ክልል ምርት አቋርጠው የነበሩ 64 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት እንዲመለሱ ማስቻሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለፁ።

ንቅናቄው የኢንዱስትሪዎችን አማካይ የማምረት አቅም ከነበረበት 44 ነጥብ 4 በመቶ ወደ 59 ነጥብ 5 በመቶ ማሳደጉንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሚያዚያ 2014 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

ንቅናቄው ኢንዱስትሪዎች የሚገጥማቸውን ማነቆዎች በመፍታት የማምረት አቅምና ምርትና ምርታማነታቸውን ከማሳደግ ባሻገር ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬ ለማዳን ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኢንዱስትሪዎች የሚገጥሟቸው የመሰረተ ልማት፣ የፋይናንስ፣ የግብዓትና የሰው ኃይል አቅርቦት ችግሮች ተለይተዋል።

በንቅናቄው እነዚህን ችግሮች በመፍታት የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ማሳደግና ዘርፉ ለሀገር እድገት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ለማስቻል በትኩረት መሰራቱንም ተናግረዋል።

ከሚመለከታቸው ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች ጋር በመቀናጀት የተሰራው ስራ የመሰረተ ልማት፣ የፋይናንስና ግብዓት አቅርቦት ችግር መፍትሄ ማግኘታቸውን ገልፀዋል።

በግንባታ ሂደት ላይ የነበሩ ኢንዱስትሪዎች በንቅናቄው በተደረገው ክትትልና ትኩረት መጠናቀቃቸውን ጠቁመው፤ በዚህ አመት ብቻ 7 ኢንዱስትሪዎች ተመርቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ንቅውናቄው ማምረት አቋርጠው የነበሩ 64 ኢንዱስትሪዎች ማምረት መጀመራቸውንና የኢንዱስትሪዎች አማካይ የማምረት አቅምም ከ44 ነጥብ 4 ወደ 59 ነጥብ 5 በመቶ ማደጉንም ገልፀዋል።

ንቅናቄው ወደ ውጪ የሚላኩ የኢንዱስትሪ ምርትና የውጭ ምንዛሬ መጠን እንዲጨምር ማድረጉንም አብራርተዋል።

ተኪ ምርቶችን በጥራትና በአይነት በማምረት ከውጭ ምርቶችን ለማስገባት ይወጣ የነበረን የውጭ ምንዛሬ ማዳን ማስቻሉን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ "ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት" በሚል የዜጎችን የሀገር ውስጥ ምርት የመግዛት ልምድ ማሳደግ የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መሰራታቻውንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ኢግዚቢሽንና ባዛሮችን በማዘጋጀት የሀገር ውስጥ ምርቶችን የማስተዋወቅና የገበያ እድል ለመፍጠር ያስቻለ እንዲሁም በኢንዱስትሪው ዘርፍ ፈርጀ ብዙ ውጤቶችን ያስገኘ እንደሆነም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም