ቀጥታ፡

በኮምቦልቻ ከተማ ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል-ከንቲባ መሐመድአሚን የሱፍ

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 23/2017 (ኢዜአ)፦በኮምቦልቻ ከተማ ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት ፈቃድ መውሰዳቸውን የከተማዋ ከንቲባ መሐመድአሚን የሱፍ ገለጹ።

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የምትገኘው ኮምቦልቻ ከተማ ከምስረታዋ 1928 ዓ.ም ጀምሮ ለኢንዱስትሪና ሎጂስቲክስ ማዕከልነት የተመረጠች ከተማ ናት።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መሐመድ አሚን የሱፍ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ከተማዋ ከምስረታዋ ጀምሮ ባለፉት ዓመታት ለአምራች ኢንዱስትሪና የሎጂስቲክስ ማዕከልነት ተመራጭ ሆና ቀጥላለች።

ኮምቦልቻ ለማዕከላዊ ገበያ ቅርብ መሆኗ እና በርካታ መሰረተ ልማት ያላት መሆኑ ተመራጭ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት መዳረሻ እያደረጋት ነው ብለዋል።

የኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ ማዕከልነት እያንሰራራ ነው ያሉት ከንቲባው፤ የአካባቢው ሰላም መሆን፣በርካታ አምራች የሰው ኃይል መኖሩ እና ለቀልጣፋ አገልግሎት የተሰጠው ትኩረት ለከተማዋ የኢንቨስትመንት ዕድገት መጨመር ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህ ዓመትም ወደ ከተማዋ ለኢንቨትመንት የመጡ ባለሀብቶች ቁጥር በከፍተኛ መጠን መጨመሩን ገልጸዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 25 ቢሊዮን 503 ሚሊዮን 729 ሺህ 401 ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

በግብርና ምርት ማቀነባበር፣በኬሚካልና ኮንስትራክሽን፣ በእንጨትና ብረታብረት፣በጨርቃጨርቅና አልባሳት፣በግብርና፣ በሆቴልና ቱሪዝም የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሠማራት 103 ባለሀብቶች ፈቃድ መውሰዳቸውን ገልጸው፥ መሬት ተረክቦ ወደ ልማት ከመግባት ጀምሮ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ሂደት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በከተማዋ በውጭ ኩባንያዎችና በሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የተከፈቱ 127 ከፍተኛ ፤መካከለኛና አነስተኛ ፋብሪካዎች በማምረት ላይ መሆናቸውንም ከንቲባው ተናግረዋል።

ፋብሪካዎቹ በዘጠኝ ወራቱ ውስጥ ለውጭ ገበያ ካቀረቧቸው ምርቶች 36 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸው፤ 73 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ተኪ ምርቶችን ለአገር ውስጥ ገበያ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

ከ10 ሺህ 600 በላይ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን የጠቀሱት ከንቲባው፤ በአሁኑ ወቅትም ተጨማሪ ከ110 በላይ ፋብሪካዎች በግንባታ ሂደት ላይ ናቸው ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩና የፌዴራል መንግሥት የመሬት፣ የኤሌክትሪክ አቅርቦትና ሌሎችም የመሰረተ ልማትና የአገልግሎት ፍላጎቶችን ፈጣን ምላሽ እየሰጡ እንዲገኙም ገልጸዋል።

የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በተኪ ምርት ላይ የጀመሩትን ሥራ የማጠናከርና የመደገፍ ተግባራትን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠቁመዋል።

ኮምቦልቻ በአምራች ኢንዱስትሪዎቿ ዕድገት ልክ የተሟላ የሎጅስቲክስ አቅም እየገነባች መሆኗንም አንስተዋል።

አሁን አገልግሎት እየሰጠ ከሚገኘው ደረቅ ወደብ በተጨማሪ የፌዴራል መንግሥት በ25 ሄክታር መሬት ላይ ሌላ ደረቅ ወደብ እየተገነባ መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማዋ ግዙፍ መጋዘኖች፣ወደ ማዕከላዊ ገበያና ወደ ባህር ወደብ የሚወስዱ አመቺ የየብስ መንገዶች መኖራቸውም የሎጅስቲክስ ማዕከል ያደርጋታል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም