የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በትውልድ ቅብብሎሽ የተገነባ ኅብረብሔራዊ ሠራዊት ነው - አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በትውልድ ቅብብሎሽ የተገነባ ኅብረብሔራዊ ሠራዊት ነው - አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 23/2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በትውልድ ቅብብሎሽ የተገነባ ኅብረብሔራዊ ሠራዊትና ተቋም መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
ሀገር አቀፍ 116ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ቀን የሲምፖዚየም እና አውደ-ርዕይ ዝግጅት "የተለወጠ ፖሊስ፥ እየተለወጠ ላለ ሀገር" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም መከበር ጀምሯል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ የኢትዮጵያ ፖሊስ በትውልድ ቅብብሎሽ የተገነባ ሠራዊትና ተቋም ነው ብለዋል።
በተጨማሪም በሀገራዊ ለውጡ ማግስት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ትልልቅ የለውጥ እርምጃዎችን ማስመዝገብ እንደቻለ ገልጸዋል።
በሠላምና ደኅንነት ተቋማት የለውጥ እርምጃ ከተወሰደባቸው ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ስኬታማ የማሻሻያ እርምጃ መውሰዱን ተናግረዋል።
በዚህም በሠራዊት ግንባታ፣በሰው ሃብት ልማት፣ በዘመናዊ ትጥቅ፣ ወንጀል መከላከልና ምርመራ ገለልተኝነቱን የጠበቀ ህዝባዊ የፖሊስ ተቋም መገንባቱን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የኢትዮጵያ፣ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን በማቀፍ ኅብረ-ብሔራዊነቱን የጠበቀ ተቋም ነው ብለዋል።
በቀጣይም ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓት እና ሀገራዊ አንድነትን በመጠበቅ፣ በወንጀል መከላከልና ምርመራ፣ በሰብዓዊ መብት ጥበቃና ሕግ የማስከበር ሀገራዊ ኃላፊነቱን በብቃት የመወጣት ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል፥ የኢትዮጵያ ፖሊስ ባለፉት 116 ዓመታት የተለያዩ ሥርዓቶችንና ህዝብን ያገለገለ ታላቅ ተቋም ነው ብለዋል።
ከሀገራዊ ለወጡ ወዲህም የፍትሕ፣ የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት በተከናወነ የሪፎርም ስራ መነሻነት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ስኬታማ የማሻሻያ እርምጃ መውሰዱን ገልጸዋል።
በዚህም በህብረተሰብ ተሳትፎ መርህን የተከተለ በወንጀል መከላከልና ምርመራ፣ ሠብዓዊ መብት ጥበቃ፣ በማስረጃና መረጃን የተመሰረተ ሕግ የማስከበር ተግባር ምስክርነት የተቸራቸው ስኬታማ ስራዎች መሰራታቸውን አብራርተዋል።
በተለይም በቴክኖሎጂ የተደገፈ የወንጀል ምርመራ በዘመናዊ የኮሙኒኬሽን ትጥቅ፣በፎረንሲክ ምርመራ፣ በሎጂስቲክስ መስክ በዘመናዊ ተሽከርካሪ መታጠቅ እንደተቻለ ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪ፣ዩኒቨርሲቲ እና የአቪዬሽን ፖሊስ አደረጃጀት በመዘርጋት ጤናማ የምርታማነት፣መማር ማስተማርና ሰላማዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት እንዲፈጠር መደረጉን አንስተዋል።
የኢትዮጵያን ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ ሂደትም ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከክልልና ከተማ አስተዳደር የፖሊስ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ስኬታማ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በቀጣይም ቀጣናዊ፣ አሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ አጋርነቱን በማስፋት ለዜጎችና ለሀገር ሰላምና ደኅንነት መጠበቅ ተምሳሌት የሆነ የፖሊስ ተቋም የመገንባት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነቱን የጠበቀ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ተቋም መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ከዛሬ ጀምሮ እስከ 25/2017 ዓ.ም ድረስ ባሉት ተከታታይ ቀናት የሚቆየው ሀገር አቀፍ 116ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ቀን የማጠቃለያ መርሃ ግብርም በሚቀጥለው ሚያዝያ 26/2017 ዓ.ም በመዲናዋ መስቀል አደባባይ በሚካሄድ በደማቅ የወታደራዊ ትርዒት ዝግጅት ፍፃሜውን የሚያገኝ ይሆናል።