ለክልሉ ጤና ቢሮ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የመድሃኒትና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ለክልሉ ጤና ቢሮ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የመድሃኒትና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ
ጋምቤላ፤ሚያዝያ 23/2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማህበር ጋምቤላ ቅርንጫፍ ለጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የመድኃኒትና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
የማህበሩ ቅርንጫፍ ድጋፉን ያደረገው ከተባበሩት መንግስታት የስነ ህዝብ ፈንድ (UNFPA) ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ መሆኑም ታውቋል።
የጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አቤል አሰፋ ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት እንዳሉት፥ የቤተሰብ መምሪያው ያደረገው ድጋፍ በጤና ተቋማት የሚስተዋለውን የመድኃኒትና የህክምና ግብዓት እጥረት ያቃልላል።
በተለይም በክልሉ በቤተሰብ እቅድና በስነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ የሚከናወኑ ስራዎችን የሚያጠናክር መሆኑን ጠቅሰው፥ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አሪያት ኡጁሉ በበኩላቸው፥ ድጋፉ በጤና ተቋማት በመድኃኒትና በህክምና ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ለችግር ለሚጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎች እፎይታ እንደሚሰጥ ገልጸው፥ ለተደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማህበር የጋምቤላ ቅርንጫፍ የስነ ህዝብ ፈንድ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ድንገቱ ማሞ በርክክቡ ወቅት እንዳሉት፥ ማህበሩ በተለይም ለስነ ተዋልዶ ጤና እና ለህፃናት ጤና አገልግሎት የሚውል ድጋፍ አድርጓል።
ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለው የመድሃኒትና ቁሳቁስ ድጋፉ በጋምቤላ ከተማ የመጀመሪያና አጠቃላይ ሆስፒታሎች፣እንዲሁም በላሬ፣ በኢታንግ፣ በአቦልና በፑቻላ ጤና ጣቢዎች የሚሰጠውን አገልገሎት ለመደገፍ ያለመ መሆኑንም ተናገረዋል።