ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከኃይል ማመንጫነቱም ባለፈ የአካባቢውን ብዝሃ ህይወት በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው

አሶሳ፤ሚያዝያ 23/2017 (ኢዜአ):- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከኃይል ማመንጫነቱም ባለፈ የአካባቢውን ሥነ ምህዳር ና ብዝሃ ህይወት በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑ ተገለጸ።

በኢትዮጵያውያን የጋራ ትጋትና ርብርብ ተገንብቶ ሊጠናቀቅ ከጫፍ የደረሰው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያም ባለፈ ለአካባቢው አገራት የላቀ ፋይዳ ያለው ነው።

ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ላይ በተፈጠሩት ከ70 በላይ ደሴቶች የቱሪዝም መስህብ ስፍራ በማድረግ ጎብኝዎች ከሚዝናኑባቸው ተመራጭ ስፍራዎች መካከል የማድረግ እድል አግኝታለች።

ከተፈጠሩት ደሴቶች ከ40 በላይ የሚሆኑት እያንዳንዳቸው ከ10 ሄክታር በላይ ቦታ የያዙ በመሆኑም ለመዝናኛ ስፍራነት፣ለብዝሃ ህይወት ጥበቃ፣ ለአካባቢ ስነ ምህዳር ውበት እና በአየር ሁኔታው ተመራጭና ምቹ የመኖሪያ አካባቢ የማድረግ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አንስተዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምህዳር እና ስነ ህይወት ትምህርት ክፍል መምህር ጌታቸው ገለታ፤የህዳሴ ግድብ በቀጣይ እየተገለጡ የሚሄዱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት ብለዋል።

የህዳሴ ግድብ ከኃይል ማመንጫነቱም ባለፈ የአካባቢውን ሥነ ምህዳር እና ብዝሃ ህይወት በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን አንስተዋል።

የአካባቢውን ሞቃታማ የአየር ንብረት በመቀየር፤ሀገር በቀል ዕፅዋቶች እንዲበራከቱ እና በዓሳ ምርትም በግንባር ቀደምትነት ሊጠቀስ የሚችል ስፍራ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።

የውሃ ሃብት የብዝሃ ህይወት መሠረት በመሆኑ በግዙፉ ባህር ላይ ህይወታቸውን የሚያደርጉ እንስሳትና አእዋፋት እንዲሁም በአካባቢው በምቾት የሚለሙ እጽዋት እምቅ ሃብቶች ይሆናሉ ብለዋል።

በኢትዮጵያ ለተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የህዳሴ ግድብ የራሱ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን አንስተው፥ ለታችኞቹ የተፋሰሱ አገራትም የጎርፍ አደጋን በመቀነስ ጉልህ ፋይዳ አለው ነው ያሉት።

ግድቡ በሚፈጥረው የሥነ ምህዳር ለውጥ አካባቢው ለቱሪስት መስህብና የመዝናኛ ኢንዱስትሪው ተመራጭ ስፍራ እንደሚሆን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል ብለዋል።

በአካባቢው የሥነ ምህዳር ለውጥ በመፍጠር፣ የአካባቢውን የተፈጥሮ ሚዛን በማስተካከል እንዲሁም የተለያዩ ብዝሃ ህይወት መገኛ ማእከል እንደሚሆንም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም