የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ 116ኛውን የኢትዮጵያ ፖሊስ ቀን ሲምፖዚየምና አውደ-ርዕይ መርቀው ከፈቱ - ኢዜአ አማርኛ
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ 116ኛውን የኢትዮጵያ ፖሊስ ቀን ሲምፖዚየምና አውደ-ርዕይ መርቀው ከፈቱ
አዲስ አበባ ፤ሚያዝያ 23/2017 (ኢዜአ)፦የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን የ116ኛውን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ቀን ሲምፖዚየምና አውደ-ርዕይ መርቀው ከፍተዋል።
ሀገር አቀፍ 116ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ቀን የሲምፖዚየም እና አውደ-ርዕይ ዝግጅቶች በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም መከበር ጀምሯል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ቀን የሲምፖዚየምና አውደ-ርዕይ ዝግጅት ከ1901 እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ "የተለወጠ ፖሊስ፥ እየተለወጠ ላለ ሀገር" በሚል መሪ ሃሳብ በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ማርች ባንድ በደማቅ የማስጀመሪያ ሥነ-ስርዓት በይፋ ተከፍቷል።
በክብረ በዓሉም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረ-ሚካኤል፣ የመከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ መኮንኖች፥ አባትና እናት አርበኞች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።
ክብረ በዓሉም ከዛሬ ሚያዚያ 23 ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 25/2017 ዓ.ም ድረስ ባሉት ተከታታይ ቀናት የኢትዮጵያን ፖሊስ ታሪካዊ አመጣጥና የተመዘገቡ ፖሊሳዊ የሪፎርም ስኬቶችን የሚያሳዩ ሲምፖዚየምና አውደ-ርዕይ ዝግጅቶች እንደሚካሄዱ ተገልጿል።
በዚህም በሳይንስ ሙዚየም በተደረገው የሲምፖዚየምና አውደ-ርዕይ ዝግጅት ላይ የኢትዮጵያን የፖሊስ ታሪክ፣ የፖሊስ ሪፎርም፣ የሰው ሃብት ልማት፣ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ፣ የወንጀል መከላከል፣ የወንጀል ምርመራ፣ የሠራዊት ግንባታ፣ በፖሊሳዊ ቴክኖሎጂ፣ ጤና አገልግሎት፣ የጀግኖች ማዕከል፣ አዲሱ የፌዴራል ፖሊስ የደንብ ልብስን ጨምሮ ተቋማዊ የምርታማነትና የለውጥ እርምጃዎች ለዕይታ ቀርበዋል።
በዓሉን በማስመልከት ከሚያዝያ 19 ጀምሮ እስከ 25/2017 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት በአበበ ቢቂላ እና አዲስ አበባ ስታዲየም በሰባት የቀጣናው ሀገራት መካከል ስፖርታዊ ውድድር በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ቀን በማስመልከትም የክልልና ከተማ አስተዳደር የፖሊስ ተቋማት በተለያዩ ዝግጅቶች ክብረ በዓሉን እንደሚያከብሩት ተመላክቷል
ሀገር አቀፍ 116ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ቀን የማጠቃለያ መርሃ ግብርም በሚቀጥለው ሚያዝያ 26/2017 ዓ.ም በመዲናዋ መስቀል አደባባይ በሚካሄድ በደማቅ የወታደራዊ ትርዒትዝግጅት ፍፃሜውን እንደሚያገኝ ተገልጿል።