ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአፋር ክልል አስር ፋብሪካዎች በቅርቡ ተመርቀው ስራ ይጀምራሉ-ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 23/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አካል የሆኑ አስር ፋብሪካዎች በአፋር ክልል በቅርቡ ተመርቀው ስራ እንደሚጀምሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ሚያዚያ 2014 ዓ.ም ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ንቅናቄው በአገር ውስጥ ተኪ ምርትንና አምራቾችን በማበረታታት የምርት ተደራሽነትን ከማስፋት በተጨማሪ አገሪቱ ከውጭ የምታስገባቸውን ምርቶች በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ በክልሉ ከለውጡ ወዲህ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።

ከተግባራቶቹ መካከልም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም በክልሉ ለሚካሔዱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሯል።

ንቅናቄው አምራች ኢንዱስትሪውን በማበረታታት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።

በተለይም ክልሉ በኢንዱስትሪ፣በግብርናና በቱሪዝም ዘርፎች ትልቅ ሃብት ያለው መሆኑን ገለጸው፤ ሀብቱን ጥቅም ላይ ለማዋል በሚደረገው ጥረት ንቅናቄው በእጅጉ እያገዘ ይገኛል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አካል የሆኑና በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ አስር ፋብሪካዎች በቅርቡ ተመርቀው በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ እንደሚገቡም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

ከተኪ ምርት አኳያም እንዲሁ ክልሉ ያለውን የጨው ሃብት ወደ ጥቅም በመቀየር ከውጭ ይገባ የነበረውን የጨው ምርት ሙሉ ለሙሉ መተካት እንደተቻለም ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል።

የጨው ምርትን በጥሬ ከማምረት በዘለለ እሴት በመጨመር የተለያዩ ኬሚካሎችን ለማምረት የሚያስችል ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑንም አክለዋል።

ይህም የጨውና ከጨው ምርት የሚገኙ ኬሚካሎችን ከአገር ውስጥ አልፎ ለውጭ ገበያ የማቅረብ ሒደቱን እንደሚያፋጥን ነው የገለጹት።

ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ቀደም ሲል በክልሉ የማይመረቱ ምርቶችንና እምቅ ሃብቶችን ለመለየት እድል ስለመፍጠሩም አንስተዋል።

የግብርና ምርታማነትን ከንቅናቄው ጋር በማስተሳሰር እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በአሁኑ ወቅት በክልሉ በፍራፍሬ ምርት አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል።

ለአብነትም ሙዝን በስፋት በማምረት የማቀነባበር ስራው ትኩረት የተሰጠው ሲሆን በቅርቡም እሴት የተጨመረበት የሙዝ ምርት ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ይሆናል ነው ያሉት።

ይህም ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለክልሉ እያስገኘ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አጉልቶ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በአፋር ክልል ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ያሉ ከ300 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም