በአዲስ አበባ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሰፋፊ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው -ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሰፋፊ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው -ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 22/2017(ኢዜአ)፦በመዲናዋ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ስፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።
የምክር ቤቱ አባላት በየመስኩ ማብራሪያ የሚሹ ጥያቄዎችን አቅርበው በከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ከመሰረተ ልማት አቅርቦት፣ የኑሮ ውድነት ማረጋጋት እንዲሁም አገልግሎት አሰጣጥ ላይ መልካም ውጤቶች መገኘቱን ያነሱት የምክር ቤቱ አባላት ዘላቂነት ላይ ይበልጥ ሊሰራ እንደሚገባም ነው ያነሱት።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሰጡት ማብራሪያ፥ ከመሰረተ ልማት አቅርቦትና የኑሮ ውድነት ከማረጋጋት እንዲሁም አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በማብራሪያቸውም ኑሮ ውድነትን ለመቀነስ በምርት አቅርቦት እንዲሁም በከተማ ግብርና ላይ ሰፋፊ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል ።
ከምርት አቅርቦት አኳያም በመዲናዋ በተገነቡ የገበያ ማዕከላት ምርትን ከአርሶ አደሩ በቀጥታ በመቀበል ለሸማቾች በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በመዲናዋ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማና ለሚኩራ ክፍለ ከተማ ቁጥር 2 የገበያ ማዕከላትን ወደ ሥራ ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ወደ ስራ የሚገቡ የገበያ ማዕከላት ገበያውን የማረጋጋት አቅምን ይበልጥ የሚያሳድጉ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ገልጸው 35 ሺህ አረጋዊያንን እና ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ ዜጎች የምገባ መርሃ ግብር ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በመዲናዋ የሚሰጠው የትራንስፖርት አገልግሎት ዜጎችን በማይጎዳ መልኩ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸው፤ ከተማ አስተዳደሩ በዓመት ከ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከንቲባዋ እንደገለጹት፥ በኮሪደር ልማት ምክንያት ለተነሱ ነዋሪዎች 9 ሺህ 700 ቤቶች ተገንብተው ተደራሽ የተደረጉ ሲሆን ለአቅመ ደካማ ዜጎችም ቤቶችን በማደስና በመገንባት የማቅረብ ሥራዎች በተሳካ መልኩ ተከናውነዋል።
347 አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታል መቀየራቸውን የገለጹት ከንቲባ አዳነች አገልግሎትን በዲጂታል የመስጠቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
የተሳለጠ አገልግሎትን ለነዋሪዎች ተደራሽ ከማድረግ አኳያም በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከመዲናዋ እድገት ጋር ተያይዞ የውሃ አቅርቦት ፍላጎት እየጨመረ መሆኑን ጠቅሰው፤ አቅርቦትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው፥ የኮሪደር ልማቱ በሁሉም አካባቢዎች ደረጃ በደረጃ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ ለ2017 በጀት ዓመት ከ11 ቢሊዮን 556 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀትንና ለተለያዩ የስራ ሃላፊዎች ሹመት በማጽደቅ ተጠናቋል።