ፕሮጀክቱ 12 ሺህ የአንድ ቀን የዶሮ ጫጩቶችን አሰራጨ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሮጀክቱ 12 ሺህ የአንድ ቀን የዶሮ ጫጩቶችን አሰራጨ

ሀዋሳ ፤ሚያዝያ 22/2017 (ኢዜአ)፡- ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የሻሎ ቅድመ ወላጅ የዶሮ ልማት ፕሮጀክት ያራባቸውን 12 ሺህ የአንድ ቀን ጫጩቶች አሰራጨ።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት በሀገር ደረጃ የተያዘውን የዶሮ እርባታ ለማስፋፋት ተግዳሮት ከሆኑት አንዱ በየጊዜው የአንድ ቀን ጫጩቶችን ከውጪ ማስገባት ነበር።
ችግሩን ለመፍታት ከተያዙ አቅጣጫዎች ውስጥ አንዱ የቅድመ ወላጅ ዶሮዎችን በሀገር ውስጥ በማርባት ማሰራጨት መሆኑን ጠቁመዋል።
የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብርን ለማሳካት በተያዘው አቅጣጫ መሰረት ቅድመ ወላጅ ዶሮዎችን በሀገር ውስጥ አባዝቶ ለአርቢ ማዕከላት ለማሰራጨት ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሀላፊነት ወስዶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራጩት የአንድ ቀን የዶሮ ጫጩቶችን የሚረከቡ አባዥ ማዕከላት አስፈላጊውን መስፈርት አሟልተው የተመረጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በዚህም ዛሬ በሲዳማ ክልል እንስሳትና አሣ ሀብት ልማት ቢሮና በአላጌ ግብርና ኮሌጅ ስር ላሉ ማእከላት 12 ሺህ የአንድ ቀን የዶሮ ጫጩቶችን ማስረከብ እንደተቻለ ገልጸዋል።
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የአግሮ ክላስተር ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፈለቀ ታደሰ እንደገለጹት ከስምንት ወራት በፊት ከሀንጋሪ ከገቡ 10 ሺህ ቅድመ ወላጅ የዶሮ ዝርያዎች የተገኙ 12 ሺህ የአንድ ቀን የዶሮ ጫጩቶችን ለመጀመሪያ ጊዜ ማሰራጨት መጀመሩን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ከዛሬ ጀምሮ በየሳምንቱ 12 ሺህ የአንድ ቀን የዶሮ ጫጩቶችን ለተመረጡ አባዥ ማዕከላት እንደሚሰራጭ አመላክተዋል።