ለአካባቢ ተስማሚ ምርቶች ለማምረትና ፕላስቲክን ለመተካት በምርምር የታገዘ ሥራ ተጀምሯል - የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 22/2017(ኢዜአ)፦ለአካባቢ ተስማሚ ምርቶች ለማምረትና ፕላስቲክን ለመተካት በምርምር የታገዘ ሥራ መጀመሩን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ በአሁኑ የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ለአካባቢ ተስማሚ ምርቶችን የማያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ከገበያ የመውጣት ዕጣ ፈንታቸው ከፍተኛ ነው።

በአገር ደረጃ መጪውን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች በስፋት እየተሰሩ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ አካባቢን የሚበክሉ የፕላስቲክ ምርቶችን ለማስቀረት የተጀመረው ስራም የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢንዱስትሪዎች ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ ምርቶችን በማምረት ፕላስቲክን የመተካት ሥራ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ይህም ከብክለት ነፃ አካባቢ በመፍጠር ዓለምአቀፍ ተቀባይነት ያለው ምርት የማምረት አካል መሆኑን በማንሳት።

በፕላስቲክ ምርት ላይ የተሰማሩ ፋብሪካዎች ሌላ ዓይነት ምርት ወደ ማምረት እንዲገቡ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግላቸውም አብራርተዋል።

ዜጎች በንጹህ አካባቢ የመኖር ህገ መንግስታዊ መብት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ለትውልዱ ንጹህ አካባቢን መፍጠር የሁሉም ድርሻ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ ኢንዱስትሪዎች ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆኑ ምርቶችን እንዲያመርቱ መደረጉ ተገቢና ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን አመልክተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም