የአፍሪካን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ የወጣቶችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ማጎልበት ይገባል -ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 22/2017(ኢዜአ)፦የአፍሪካን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ የወጣቶችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳደጉ የስታርት አፕ እና ኢኖቬሽን ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ፡፡

"ኢኖቬሽን አፍሪካ 2025" የአፍሪካ የትምህርት፣ አይ ሲ ቲ እና ክህሎት የሚኒስትሮች ስብሰባ " በ21ኛው ክፍለ ዘመን አፍሪካን ማስተማርና ማብቃት" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው።

የትምህርት ሚኒስቴር፣የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከአፍሪካን ብሬይን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት አህጉራዊ ጉባኤ ዛሬ ይጠናቀቃል።

የኢኖቬሽን አፍሪካ 2025 ጉባኤ አፍሪካን በትምህርት፣ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በክህሎት ልማትና ሥራ ፈጠራ ለማስተሳሰር ያለመ ነው።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል "ለክህሎት ልማትና አዲስ መወዳደሪያ ለአፍሪካ አፍላቂዎች እና ሥራ ፈጣሪዎች" በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሄደው የፓናል ውይይት ላይ ንግግር አድርገዋል።

ሚኒስትሯ በመክፈቻ ንግግራቸው፤የኢኖቬሽን አፍሪካ 2025 ጉባኤ በኢንዱስትሪዎች፣ ሲቪል ማህበራት፣ በትምህርት ተቋማት መካከል ትብብር በመፍጠር ክህሎትን ለማሳደግ እና የፖሊሲ ግብዓት ለማሰባሰብ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ እና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በማድረግ ብልፅግናን ለማረጋገጥ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለበርካታ ወጣቶች የክህሎት ሥልጠና በመስጠት ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ወጣቶችን ማፍራት የሚያስችል አሰራር ስርዓት ተዘርግቶ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።

የዓለም የሥራ ፈጠራ ገበያ ውድድር የበዛበት መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ የወጣቶችን የፈጠራ አቅም ማጎልበትና ማበረታታት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በእያንዳንዱ የቴክኒክ እና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከላትን በማስፋፋት ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ ምቹ ሥነ ምህዳር መፍጠር መቻሉንም ገልጸዋል።

በአፍሪካ ወጣቶች በስራ ፈጠራ፣ኢኖቬሽን እና ክህሎት ልማት የላቀ ሚና እንዲኖራቸው ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል።

የሥራ ፈጠራ ለወጣቶች ከእለት ፍጆታ ባለፈ መሆን አለበት ያሉት ሚኒስትሯ፣ አዳዲስ የፈጠራ ክህሎትን ማዳበር ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።

በአፍሪካ አካታችና ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት በግብርና፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም፣ አይ ሲ ቲ ዘርፎች ላይ ክህሎትን ማስታጠቅ እና ማብቃት ይገባል ብለዋል።

የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት መተባበር እና የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎን ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የኮንጎ ሪፐብሊክ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ሚኒስትር ፕሮፌሰር ጊስላን ማጉሳ ኢቦሜ በበኩላቸው ሀገራቸው የወጣቶችን የዲጂታል ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የነደፈችው ስትራቴጂ ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ኮንጎ ሪፐብሊክ በዓመት ከ200 እስከ 300 ሺህ ወጣቶች ኢንተርፕራይዞችን እንዲቀላቀሉ እቅድ ተይዞ ጥሩ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል፡፡

በአፍሪካ የወጣቶች የሥራ እድል ፈጣራ ሀገራቸው የተሻለ ልምድ እንዳላት የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በየክልሉ የኢንተርፕራይዞች ፎረም በማካሄድ ወጣቶች እውቀታቸውንና የሀገራቸውን ሀብት እንዲገነዘቡ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

በዚህም የዲጂታላይዜሽን ሥራ ፈጠራ ከነበረበት አዝጋሚ ለውጥ በፍጥነት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

የሶማሊያ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዩሱፍ ሞሀመድ አዳን ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂን በመጠቀም በወጣቶች ክህሎት በማበልጸግ አስገራዊ ለውጥ አምጥተናል ብለዋል፡፡

የወጣቶችን ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረገ ብሔራዊ የሥራ ፈጠራ ማዕከል በመገንባት ሥልጠናና የዲጂታል ትምህርት መስጠት ጀምረናል ሲሉም አክለዋል።

በተለይም ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር ወጣቶችን በታዳሽ ሀይል እና በሥራ ፈጠራ ላይ በቂ ግንዛቤ በማስጨበጥ ወደ ስራ ማስገባታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከአፍሪካ ልማት ባንክ እና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበርም የገጠር ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንቅስቃሴ እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም