በክልሉ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂና የምርምር ሥራዎችን ሊያጠናክሩ ይገባል

ቦንጋ፤ሚያዚያ 22/2017 (ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ የቴክኖሎጂና ምርምር ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባቸው ተገለፀ።

የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ ''ብሩህ አዕምሮዎች፣ በክህሎት የበቁ ዜጎች'' በሚል መሪ ቃል የክህሎት፣የቴክኖሎጂና የተግባራዊ ጥናትና ምርምር ውድድርና አውደ ርዕይ በቦንጋ ከተማ ማካሄድ ጀምሯል።

የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ በወቅቱ እንደገለጹት፣ በክልሉ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት በቴክኖሎጂና ምርምር ዘርፍ የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ሥራዎችን ማፍለቅ ይጠበቅባቸዋል።

ይህን እውን ለማድረግም ለተቋማቱ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል ።

ተቋማቱ በስነምግባር የታነፀ የፈጠራ ክህሎት ያለው የሰው ኃይል በማፍራትና ዘርፉ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያደርግበትን አቅም መፍጠር ላይ ተጨማሪ ስራ መስራት እንደሚጠይቅም አመልክተዋል።

የቴክኒክና ሙያ ማስልጠኛ ተቋማቱ የክልሉን የልማት ጸጋ ማዕከል ያደረገ ብቁ የሰው ሀይል ማፍራትና ቴክኖሎጂን መቅዳት ላይ አተኩረው እንዲሰሩ የሚደረገው ጥረት እንደሚጠናከር የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አብይ አንደሞ ( ዶ/ር) ናቸው።

የክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራን ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ ከስልጠና በተጨማሪ በምርምር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ቤቴልሔም ዳንኤል በበኩላቸው፥ በክልሉ የሚካሄደው ሁለተኛ ዙር የክህሎት፣ቴክኖሎጂና የተግባራዊ ጥናትና ምርምር ውድድርና አውደርዕይ የትምህርት ተቋማቱ በክህሎት፣በቴክኖሎጂና በፈጠራ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋን ለማፍራት የሚያደርጉትን ጥረትን የሚያግዝ ነው።

ለሁለት ተከታታይ ቀናት በሚቆው ውድድር በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የተሰሩ የተለያዩ የቴክኖሎጂ፣የፈጠራ እና የምርምር ስራዎች የቀረቡ ሲሆን አሸናፊ ለሚሆኑት ማበረታቻ ሽልማትና ዕውቅና እንደሚሰጥ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም