አፍሪካውያን ከአጋር አካላት ጋር የሚኖራቸው ትብብር ከብሔራዊ ጥቅማቸውና ፍላጎታቸው ጋር የተጣጣመ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው - የትምህርት ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካውያን ከአጋር አካላት ጋር የሚኖራቸው ትብብር ከብሔራዊ ጥቅማቸውና ፍላጎታቸው ጋር የተጣጣመ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው - የትምህርት ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 22/2017(ኢዜአ)፦አፍሪካውያን የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከአጋር አካላት ጋር የሚኖራቸው ትብብር ከብሔራዊ ጥቅማቸውና ፍላጎታቸው ጋር የተጣጣመ መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለባቸው የትምህርት ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ።
"በ21ኛው ክፍለ ዘመን አፍሪካን ማስተማርና ማብቃት" በሚል መሪ ሀሳብ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ኢኖቬሽን አፍሪካ 2025 ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል።
የትምህርት ሚኒስቴር፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከአፍሪካን ብሬን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት አህጉራዊ ጉባኤ በአፍሪካውያን በትምህርት፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፣ በስራ ፈጠራ እና ስታርት አፕ ሪፎርም፣ አቅም ግንባታ እና ስትራቴጂካዊ ትብብር መፍጠር በሚችሉባቸው ጉዳዮች መክሯል፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) በማጠቃለያ መርሀ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ ጉባኤው የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በመሰረተ ልማትና መምህራን አቅም ግንባታ ላይ ገንቢ ውይይት የተደረገበት ነው።
በጉባኤው ላይ የተነሱ ሀሳቦች የመምህራንን አቅም ለመገንባትና የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ሊኖር ስለሚገባው ትብብር መፍትሔ የሚያስቀምጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ትምህርት የሁሉም ነገር ቁልፍ መሆኑን ገልጸው፤ በመደበኛ ትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በትምህርት መሰረተ ልማት እና መምህራን አቅም ግንባታ ተጨባጭ ስራ ጀምራለች ብለዋል።
የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል እና የመምህራንን አቅም በመገንባት የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ የሚያስችል እንቅስቃሴ እያደረገች መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በአፍሪካ ዘላቂና ጥራት ያለው የልጆች ትምህርት ስርዓት ለመገንባት አቅም ግንባታ፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ የአጭርና ረጅም ዘመን እቅድ ሊኖር እንደሚገባ ገልጸዋል።
አፍሪካ በተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ ከሁኔታዎች ጋር መራመድ ካልቻለች የከፋ ነገር ሊገጥማት እንደሚችል ነው ያብራሩት።
ዘመኑን የዋጀ ዝግጅት በማድረግ ለቀጣዩ ትውልድ የተመቸች አፍሪካን እውን ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።
አፍሪካውያን ከአጋር ተቋማት ጋር ያላቸው ትብብር መጠናከር ያለበት ቢሆንም፤ ከአህጉሪቷ ብሔራዊ ጥቅም አኳያ መቃኘት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡