በክልሉ በ“ትምህርት ለትውልድ“ ንቅናቄ ውጤት መመዝገቡ ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በ“ትምህርት ለትውልድ“ ንቅናቄ ውጤት መመዝገቡ ተገለፀ

ደሴ፤ ሚያዚያ 22/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በ“ትምህርት ለትውልድ“ ንቅናቄ ውጤት መመዝገብ መቻሉን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለፀ።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ የ2017 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት እቅድ ግምገማ መድረክ በደሴ ከተማ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የክልሉ ማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) እንደገለጹት ጽንፈኛው ኃይል ፀረ ትምህርት እንቅስቃሴ በማድረግ የመማር ማስተማሩን ሂደት እያወከው ይገኛል፡፡
ይሁን እንጂ ቢሮው ከህብረተሰቡና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በየደረጃው የ“ትምህርት ለትውልድ“ ንቅናቄ በማካሄድ ተማሪዎች እንዲማሩና የትምህርት ጥራቱ እንዲጠበቅ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ከየካቲት 3 እስከ መጋቢት 30/2017 ዓ.ም ብቻ በተደረገ ሦስተኛው ዙር ንቅናቄ በፀጥታ ችግር ተዘግተው የነበሩ 112 ትምህርት ቤቶችን ስራ በማስጀመር ከ89 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ማምጣት እንደተቻለ ገልፀዋል፡፡
በዚህም ተማሪዎች ያልተማሩትን ትምህርት በማካካስ ጭምር የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችሉ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ለክልላዊና ሀገር አቀፍ ፈተናዎችም ዝግጅት እየተደረገ በመሆኑ ሁሉም በየደረጃው የትምህርት ዘርፉን በመደገፍ ለውጤት ሊያበቃ ይገባል ሲሉም አመልክተዋል፡፡
የሰሜን ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰጠ ታደሰ በበኩላቸው፤ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በ“ትምህርት ለትውልድ“ የንቅናቄ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል፡፡
በሦስተኛው ዙር የንቅናቄ መድረክ ብቻ ከ20 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ መመለስ መቻሉን ጠቁመው፤ አሁን ላይ በተረጋጋ ሁኔታ የመማር ማስተማር ስራውን ማከናወን እንደተቻለም ጠቁመዋል፡፡
''በየደረጃው ለትምህርት በተሰጠው ትኩረት የመማር ማስተማር ስራው እየተሻሻለ መጥቷል'' ያሉት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አለምነው አበራ ናቸው፡፡
በዞኑ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል፣ ግብዓት በማሟላትና በሌሎችም የትምህርት ጥራቱን ለማስጠበቅ እየተሰራ ሲሆን ለክልላዊና ሀገራዊ ፈተናዎችም በስፋት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በዜጎች ላይ እገታና ግድያ በመፈፀም እና የትምህርት ሂደትን በማወክ በመምህራን ላይ በደልና ግፍ እያደረሰ ባለው ፅንፈኛ ቡድን ላይ የተጠናከረ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) መግለፃቸው ይታወሳል።