በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል እየተሰራ ነው

ጂንካ፤ሚያዚያ 22/2017(ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ እና በአካባቢ ብክለት የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከል በቅንጅት እየተሰራ ነው።

በክልሉ ''የእንስሳት እና የአካባቢ ጤና በመጠበቅ የማህበረሰቡን ጤና መጠበቅ!" በሚል መሪ ሀሳብ የ''አንድ ጤና'' ፕሮግራም እየተተገበረ ነው።

በአንድ ጤና ፕሮግራም የክልሉ ጤና ቢሮ፣የግብርና ቢሮ፣ የደንና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ፣የውሃ፣ የማዕድንና ኢነርጂ፣ መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመቀናጀት እየሰሩ ይገኛሉ።

በተፈጠረው ቅንጅታዊ አሰራርም ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ እና በአካባቢ ብክልት ምክንያት የሚከሰቱ ተዛማች በሽታዎችን ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ ነው።

ይህን ለማስፈጸም በጂንካ ከተማ በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ፤ተላላፊ ከሆኑ በሽታዎች 60 በመቶ የሚሆኑት ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እነዚህን በሽታዎች ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ወሳኝ መሆኑንም ነው የገለጹት።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የ''አንድ ጤና'' ፕሮግራም ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር አዲሱ እዮብ እንደገለጹት በክልሉ እየተተገበረ ያለው "የአንድ ጤና" ፕሮግራም በሽታን ቀድሞ ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ይበልጥ ውጤታማ አድርጎታል።

በክልሉ የአንድ ጤና ፕሮግራም ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ለውጦች መታየታቸውንም አመልክተዋል።

በቅርቡ በደቡብ ኦሞ፣ በጋሞ እና በጎፋ ዞኖች የተከሰተው የእንስሳት በሽታ በሰውና በእንስሳት ላይ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል በጥቂት ቀናት ውስጥ መቆጣጠር የተቻለበት ሁኔታ የቅንጅታዊ ስራው ውጤት ማሳያ መሆኑን ጠቅስዋል።

ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ አባ ሰንጋ፣ የእብድ ውሻ በሽታ፣ የበግና ፍየል በሽታ፣ የሀሩራማ ትኩሳት በሽታ እና የአዕዋፋት በሽታ እንደሚገኙበትም ተናግረዋል።

በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፈውን በሽታ ለመከላከል ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ እንስሳት የአባ ሰንጋ፤ ከ3 ሺህ 800 በላይ ለሚሆኑ ውሾችም የበሽታ መከላከያ ክትባት መሰጠቱን ገልጸዋል።

በቀጣይም "የአንድ ጤና" ፕሮግራምን እስከ ቀበሌ መዋቅር ድረስ በማውረድ ፕሮግራሙን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ሀብቴ በበኩላቸው እንደገለጹት ቢሮው የአንድ ጤና ፕሮግራም ውጤታማ እንዲሆን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

የእንስሳት የሕክምና መስጫ ተቋማትን ከመገንባት ጀምሮ የህክምና ግብአቶችን በሟሟላት እንዲሁም ለጤና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ለፕሮግራሙ ስኬታማነት የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በቀጣይም ፕሮግራሙን በክልሉ አርብቶ አደር አካባቢዎች ተደራሽ በማድረግ ተዛማች በሽታዎችን ለመከላከል የተጀመረው ጥረት እንደሚጠናክርም ተናግረዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ ቅንጅታዊ ሥራዎችን የሚያጠናክሩ ስምምነቶች የተደረጉ ሲሆን ጠንካራ የአሰራር ስርአት ለመተግበር እንዲያስችልም የስትሪንግ ኮሚቴ ተቋቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም