በክልሉ ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተማሪዎችን የማብቃት ሥራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተማሪዎችን የማብቃት ሥራ እየተከናወነ ነው

ጎንደር፤ ሚያዚያ 22/2017 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል በትምህርት ዘመኑ ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የሚቀመጡ ከ99 ሺህ በላይ ተማሪዎችን የማብቃት ሥራ በርብርብ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው የዘጠኝ ወራት የትምህርት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በጎንደር ከተማ ተካሄዷል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ መኳንንት አደመ እንደተናገሩት፤ በክልሉ እየሰፈነ በመጣው ሠላም በመታገዝ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻልና ለማብቃት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
ተፈታኝ ተማሪዎችን በተሟላ መንገድ ለሀገር አቀፉ ፈተና ለማብቃት እየተደረገ ባለው ክልላዊ ንቅናቄም ህብረተሰቡ፣ አጋር አካላት፣ ወላጆች እንዲሁም የትምህርት አመራሩ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ለአዳር ጥናት ምቹ ሁኔታን በመፍጠር፣ የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት፣ ቤተ መጽሃፍትና ቤተ ሙከራዎችን በማደራጀትና በግብዓት በማጠናከር ተማሪዎች የተሟላ ዝግጅት እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በመቋቋም 3 ሚሊዮን የሚጠጉ መደበኛ ተማሪዎችን በመመዝገብ ወደ ትምህርት ገበታ ማምጣት እንደተቻለም አስረድተዋል፡፡
''ትምህርት የቀጣይ ትውልድ ግንባታ መሰረት ነው'' ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው በቀሪ ወራቶች በትምህርቱ ዘርፍ የታቀዱ ተግባራትን ለማስፈጸም ህብረተሰቡና የትምህርት አመራሩ ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
''የትምህርት ጥራትን ሽፋንና ፍትሃዊ ተደራሽነትን በማረጋገጥ ተማሪዎችን ለውጤት ለማብቃት ከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እየሰራ ነው'' ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ነጋሽ ናቸው፡፡
በዘንድሮ የትምህርት ዘመን በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ 16 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ3 ሺህ 500 በላይ ለሀገር አቀፍ ፈተና የሚቀመጡ ተማሪዎችን ለማብቃት የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
ህብረተሰቡ ለ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ለሚሰጠው የማጠናከሪያ ትምህርት የሚውል ከ100 ሺህ ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ በማዋጣት ድጋፍ ማበርከቱንም ተናግረዋል፡፡
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ክንዱ ዘውዱ በበኩላቸው፤ በሀገር አቀፉ የ12ኛ ክፍል ፈተና ላይ የሚቀመጡ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እገዛ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በዘንድሮ የትምህርት ዘመንም በ29 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ8 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስፈተን የማጠናከሪያ ትምህርትን ጨምሮ የአዳር ትምህርት ፕሮግራሞች ተዘጋጅተው ተማሪዎችን የማብቃት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው የግምገማ መድረክ ላይም የጎንደር ከተማን ጨምሮ ከማዕከላዊ፣ ከሰሜንና ከምእራብ ጎንደር ዞኖች የተውጣጡ ሱፐርቫይዘሮች፣ ርዕሳነ መምህራን፣ አጋር አካላትና የትምህርት አመራሮች ተሳታፊ ናቸው፡፡