በመተማ ወረዳ የሰሊጥና የአኩሪ አተርን ምርታማነት ለማሳደግ ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመተማ ወረዳ የሰሊጥና የአኩሪ አተርን ምርታማነት ለማሳደግ ዝግጅት እየተደረገ ነው

ገንዳ ውሃ፤ሚያዝያ 22/2017(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል መተማ ወረዳ በመኸር ሰብል የሰሊጥና የአኩሪ አተርን ምርታማነት ለማሳደግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
የአካባቢው አርሶ አደሮች በበኩላቸው ለዘንድሮው መኸር እርሻ የተሻለ ምርት ለማግኘት የሚያስችል የመሬት ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ ጌትነት ካሳሁን፤ በዞኑ ለመኸር አዝመራው እየተደረገ ያለውን ዝግጅት በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በዞኑ በተለይም የሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ማሽላ፣ ጥጥ፣ ማሾ እና ሌሎችም ሰብሎችን ማምረት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መኖሩን ገልጸዋል።
በዚሁ መሰረት በ2017/18 የምርት ዘመን 530 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ከታቀደው እስካሁን ከ345 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለዘር ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በተያዘው የመኸር ወቅትም 12 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት የማግኘት ግብ መያዙን አንስተው ከመሬት ዝግጅት ባለፈ የግብርና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ግብዓቶችን የማቅረብና የሜካናይዜሽን እርሻን የማጠናከር ስራ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን አንስተዋል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ አርሶ አደር ጋሻው ፈረደ፤ በዘንድሮው የመኸር ወቅት የመሬት ዝግጅት በማድረግ የተሻለ ምርት ለማግኘት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ 10 ሄክታር መሬታቸውን በሰሊጥ፣አኩሪ አተር፣ማሽላና የጤፍ አዝእርት ለመሸፈን ያቀዱ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመተማ ወረዳ በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩት አቶ አብርሃም ሲሳይ በበኩላቸው፤ በመኸሩ ከ60 ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ለዘር ዝግጁ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ ባለፈው ዓመት የምርት ዘመን 521 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።