በትጥቅ የሚደረግን የጥፋት መንገድ በማስቀረት በንግግር ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር በመንግስት እየተደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው

ጎንደር፤ሚያዚያ 22/2017(ኢዜአ)፦በትጥቅ የሚደረግን የጥፋት መንገድ በማስቀረት በንግግር ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር በመንግስት እየተደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን በምእራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውሃ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች ተናገሩ።

በገንዳ ውኃ ከተማ አስተዳደር "የጥፋት ክንዶችና መዘዛቸው" በሚል መሪ ሃሳብ ከመንግሥት ሰራተኞች ጋር የምክክር መድረክ ተካሄዷል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ አራጋው ፈንታ፤በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ወንጀል እየፈፀመ ያለው ፅንፈኛ ቡድን ብዙ ነገሮችን እያስተጓጎለና ሰዎችንም እየጎዳ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም የታጠቁ ቡድኖች የህዝብ የሰላም ስጋት በመሆናቸው በየአካባቢው ብዙዎች ለምሬትና እንግልት ተዳርገናል ያሉት አቶ አራጋው የመንግስት የሰላም ጥሪ በመቀበል ዘላቂ ሰላም እንዲፈጥሩ ጠይቀዋል።

የትኛውንም አይነት የፖለቲካ ጥያቄ የሚያነሳ አካል ጠመንጃውን አውርዶ የውይይት አማራጭን እንዲከተል በመንግስት እየቀረበ ላለው ተደጋጋሚ ጥሪም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ሌላኛው የመንግስት ሰራተኛ አቶ ያዜ ሽባባው እና ወይዘሮ ወርቄ ዋኘው፤ በህዝብ ላይ ዘረፋ፣ እገታ እና ግድያ እየፈፀሙ ያሉ የታጠቁ የጥፋት ቡድኖችን ከጸጥታ ሃይሉ ጎን በመሆን በጋራ መታገል አለብን ብለዋል።

የጥፋት አማራጭን በመከተል በህዝብ ላይ በደል እየፈፀመ ያለ ፅንፈኛ ቡድን ከድርጊቱ እንዲታቀብና የመንግስትን የሰላም ጥሪ እንዲቀበልም ጠይቀዋል።

የገንዳ ውኃ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አብዱልከሪም ሙሀመድ፤የህዝብና የመንግስት ትብብር በተጠናከረ መልኩ ከቀጠለ የማይፈታ ችግር የማይጋለጥና ተጠያቂ የማይሆን ወንጀለኛ አይኖርም ብለዋል።

በመሆኑም የከተማዋን ብሎም የአካባቢውን ሰላም በጋራ በማስጠበቅ ልማታችንን ለማስቀጠል ጥረታችን ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።

በዚህ ረገድ በተለይም የመንግስት ሰራተኛው ድርብ ሃላፊነት ያለው መሆኑን አንስተው፥ ለሰላምና ልማት እጅ ለእጅ ተያይዘን መስራት ይገባናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም