በአማራ ክልል ዘንድሮ በተገነቡ የውሃ ተቋማት ከ300 ሺህ በላይ ነዋሪዎች የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ሆነዋል

ባህር ዳር፤ሚያዚያ 22/2017(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል ዘንድሮ በተገነቡ የውሃ ተቋማት ከ300 ሺህ በላይ ነዋሪዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መሆናቸውን የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸምና በተሻሻለው የከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎቶች አዋጅና ደንብ ላይ የሚመክር መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ጥላሁን ሽመልስ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ በክልሉ የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል።

ለዚህም ዘንድሮ በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በጀት አንድ ሺህ 257 አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በመገንባት ላይ ካሉት ፕሮጀክቶችም 866 አነስተኛና መካከለኛ እንዲሁም 15 ከፍተኛ የውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራ ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃታቸውን ተናግረዋል።

በእነዚህ የውሃ ተቋማትም ከ300 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ የገለጹት አቶ ጥላሁን፣ የክልሉን የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን አሁን ካለበት 75 በመቶ በ1 ነጥብ 7 በመቶ ለማሳደግ ተችሏል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም