የሎጂስቲክስ ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግና ለማዘመን እየተሰራ ነው -ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 22/2017(ኢዜአ)፦የሎጂስቲክስ ሴክተሩ የሚሠጠውን አገልግሎት ይበልጥ ለማሳደግና ለማዘመን እየተሰራ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ ገለጹ።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የሎጅስቲክስ ሴክተሩ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በዘርፉ ከተሰማሩ የግል ተቋማት ሃላፊዎች ጋር ምክክር አካሂዷል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታው ደንጌ ቦሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የሎጂስቲክስ ሴክተሩ የሚሠጠውን አገልግሎት ለማሳደግና ለማዘመን የተጠናከሩ ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው።


 

በተለይም ዘርፉ እያደገ የመጣውን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ማስተናገድ እንዲችል አገልግሎት አሰጣጡን ማሳደግ የሚያስችል ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።

እንዲሁም በመስኩ የተሰማሩ ኩባንያዎች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በየደረጃው ምላሽ እንዲያገኙ በማድረግ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም ሴክተሩ ፈጣን፣ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ እንዲሆን በቅንጅት መስራት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አማካሪ መንግስቴ ኃይለማርያም (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በሎጂስቲክስ ዘርፉ ተመዝግበው የሚሰሩ አካላት ያላቸውን ተሳትፎ ለማየትና ለማሳደግም ምክክሩ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

ባለፉት አምስት አመታት በሎጂስቲክስ ዘርፉ ላይ ለውጦች የተመዘገቡ ሲሆን በቀጣይም በመስኩ የተሰማሩ ተቋማት የዘርፉን ተለዋዋጭ ባሕሪ ታሳቢ በማድረግ መስራት እንዳለባቸውም አንስተዋል።

የኢትዮ ሎጂስቲክስ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት ኤልሳቤጥ ጌታሁን በበኩላቸው፤ የሎጂስቲክስ ዘርፉን ለማሳደግ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር የሚከናወኑ ተግባራት ለውጥ እያመጡ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም