በጌዴኦ ዞን ያረጁ የቡና ዛፎችን ነቅሎ በተሻሻለ ዝርያ የመተካት ሂደት ምርታማነት እንዲጨምር አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በጌዴኦ ዞን ያረጁ የቡና ዛፎችን ነቅሎ በተሻሻለ ዝርያ የመተካት ሂደት ምርታማነት እንዲጨምር አድርጓል

ዲላ፤ ሚያዝያ 22/2017 (ኢዜአ)፡- በጌዴኦ ዞን ያረጁ የቡና ዛፎችን ነቅሎ በተሻሻለ ዝርያ የመተካት ሂደት የምርት ጊዜን ከማሳጠር ባለፈ ምርታማነት እንዲጨምር እያደረገ መሆኑ ተገለጸ።
በዞኑ የዘንድሮ የቡና ችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ በኮቾሬ ወረዳ ሐንጫቢ ቀበሌ ተካሄዷል።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት በዞኑ ከ75 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ተክል የተሸፈነ ነው።
በዞኑ ያረጀና በበሽታ የተጠቃ ቡና ለምርታማነት ማነቆ መሆኑን ጠቅሰው ችግሩን ለማቃለል በቡና እድሳት ላይ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ ያረጀ ቡና ነቅሎ በተሻሻለ ዝርያ የመተካት ጥረት የምርት ጊዜን ወደ ሁለት ዓመት ከማሳጠር ባለፈ በሞዴል አርሶ አደሮች ማሳ ከፍተኛ ምርት እያስገኘ መሆኑን አመልክተዋል።
በዞኑ ከ4 ሺህ 200 ሄክታር በላይ ማሳ ላይ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው የቡና ችግኞች ተከላ መጀመሩን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ታጠቅ ዶሪ ናቸው።
በዞኑ ለዘንድሮ የቡና ተከላም ከ11 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኝ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል ።
የኮቾሬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ታሪኩ በበኩላቸው "በወረዳው በተያዘው ዓመት ከ525 ሄክታር በላይ ነባር ማሳ ላይ ያረጁ የቡና ዛፎችን በማንሳት በተሻሻሉ ዝርያዎች ለመተካት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል" ብለዋል።
በተለይ ሐንጫቢን ጨምሮ የቡና ዛፍ እርጅና በስፋት በሚስተዋልባቸው አራት ቀበሌዎች ያረጀ ቡና በኩታ ገጠም የማንሳቱ ተግባር በትኩረት መከናወኑን ገልጸዋል።
በወረዳው የሐንጫቢ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ውዴ መላኩ በበኩላቸው ''ያረጀ አባት ቡና ይዞ መቀመጥ ትርፉ ድካም ነው” ብለዋል።
ከአንድ ሄክታር ማሳቸው ላይ ያረጀ የቡና ዛፍ በመንቀልና ከአንድ ሺህ በላይ ጉድጓዶች በማዘጋጀት የተሻሻሉ የቡና ዝርያ የመተካት ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።